ቀሪ የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራዎችን ለመሥራት ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

24
አዲስ አበባ፡ ነሐሴ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት የትግራይ ሕዝብን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቅርቧል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እየተሠሩ ያሉ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ ከሐምሌ 22 እስከ 24/2017 ዓ.ም ድረስ ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ተገኝቶ ለምክክሩ አስቻይ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረጉን ገልጸዋል። በክልሉ የተሳታፊ እና የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራውን ለማስቀጠል በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ቃል አቀባዩ አስገንዝበዋል። ለምክክሩ ውጤታማነት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።
ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ ጋር የሚደረጉ የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራዎችን በተመለከተ ኮሚሽኑ በአፍሪካ የተለያዩ ሀገሮች ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በበየነ መረብ ውይይቶችን ማካሄዱ ተገልጿል። በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሚካሄደው የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በተገኙበት ነሐሴ 3/2017 ዓ.ም እንደሚጀመር የገለጹት ቃል አቀባዩ በተመሳሳይ ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ በሰሜን አሜሪካ ለማካሄድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም ጠቁመዋል።
የሀገር በቀል ሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ሚና ይበልጥ ለማጎልበት የሚያስችል ውይይት መደረጉንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። ኮሚሽኑ የመገናኛ ብዙኃን እና የኮሙዩኒኬሽን ተቋማት በምክክሩ ሂደት ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምሥጋና አቅርቧል።
ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል ፣ ቡሔ፣ እንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ ትውፊት ብቻ ሳይኾኑ ቅርስ ናቸው።
Next articleየብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት መግለጫ