
ባሕር ዳር: ነሐሴ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ በክረምት ወራት የሚከበሩ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላትን ምክንያት በማድረግ መግለጫ ሰጥቷል።መግለጫውን የሰጡት የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ የአማራ ክልል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጎብኝዎች የሚታደሙባቸው በርካታ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላት የሚከበሩበት ክልል ነው ብለዋል።
ዓመት ጠብቀው የሚመጡት በዓላት የአማራ ክልልን ሕዝብ ባሕል እና እሴት በመጠበቅ ትውልዱ በጠንካራ ማንነት ላይ እንዲቆም ሚናቸው ከፍተኛ መኾኑንም ገልጸዋል።በዓላቱ በታሪክ ሂደት በተቀረጹበት የተለየ እና ተወዳጅ ክዋኔ ምክንያት ሚሊዮኖች በጉጉት እና በፍቅር የሚጠብቋቸው፣ የሚታደሙባቸው ሀብቶች ናቸው ብለዋል። በዓላቱ በሚከበሩበት አካባቢ ከፍተኛ ምጣኔ ሀብታዊ መነቃቃት በመፍጠር የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንዲኾን ያደርጋሉ ነው ያሉት፡፡
በክረምት ወቅት የሚከበሩት ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ ቡሔ፣ እንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ ክብረ በዓላት የተለያዩ የዕድሜ ክልል የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚያሳትፉ መኾናቸውን አንስተዋል፡፡ የተሳትፎ ሁኔታው በዕድሜ ወይም በጾታ አንዳንድ ጊዜ ገደብ ይኑረው እንጂ የበዓሉ ተሳታፊዎችን በማጀብ፣ በማስተናገድ እና በመመረቅ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ይሳተፋል ነው ያሉት፡፡
አሸንድዬ፣ ሻደይ፣ ሶለል፣ ከሴ አጨዳ እና እንግጫ ነቀላ ልጃገረዶች ባሕላቸውን እና ትውፊታዊ አደራቸውን በአደባባይ ለትውልድ የሚያስረክቡበት፣ ነፃነታቸውን አውጀው በልዕልና ዙፋን የሚነግሱበት ተወዳጅ በዓላት ናቸው ብለዋል። “ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ ብሔ፣ እንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ ባሕል ብቻ ሳይኾኑ ታሪክ፣ ትውፊት ብቻ ሳይኾኑ ቅርስ፣ ዛሬ የተጀመሩ ሳይኾኑ ጥንትም የነበሩ ዐብይ በዓላት ናቸው ነው ያሉት።
በዓላቱ አስደናቂ ባሕላዊ ትዕይንቶች በዓለም አደባባይ ከፍ ብለው የሚታዩበት፣ የማይጠገብ የጥበብ ድግስ አዘጋጅተው፣ ተሰምቶ የማይሰለች ባሕልና ታሪካቸውን አደባባይ ወጥተው የሚያሳዩበት ባሕላዊ ክዋኔ እና የቱሪዝም መስህብ መኾናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ክብረ በዓላቱ በአግባቡ ለምተው እና ተጠብቀው ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ እና ወደ ቱሪዝም ገበያው እንዲገቡ በመሥራቱ ውጤት እየተመዘገበ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ለአብነትም በሚከወኑበት አካባቢ ብቻ ተወስነው የቆዩትን የቡሔ፣ የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል እና የእንግጫ ነቀላ በዓላት በክልል ደረጃ በማክበር እና በማስተዋወቅ ከፍተኛ ተቀባይነትን እንዲያገኙ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
ክብረ በዓላቱ የተስፋ በዓላት እንደኾኑ ይታመናል ያሉት ኀላፊው የነገ ተስፈኞች ሻደይ ፣አሸንድዬ እና ሶለል በዓላት ልጃገረዶች በአደባባይ ወጥተው የሚቦርቁበት፣ የተስፋ ምልክት የኾነውን አረንጓዴ ሣር ወይም አሸንድዬን በለጋ ወገባቸው አስረው የሚደስቱበት እንደኾኑ ነው የገለጹት፡፡ ከሴ እና እንግጫ በመንቀልም አዲስ ዓመት መቃረቡን ማብሰሪያ እንደኾነም ተናግረዋል::
የዘንድሮው በዓል “ባሕላዊ ዕሴቶቻችን ለዘላቂ ሰላማችን የነበርንበት፣ ያለንበት እና የምንደርስበት” በሚል መሪ መልዕክት እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡ መልዕክቱ በዓላቱ አስቀድመው የነበሩን፣ አሁንም እየተከወኑ ያሉ እና ወደፊትም ተጠብቀው ለትውልድ የሚተላለፉ መኾኑን ለማመላከት ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ዓመትም ቡሔ በደብረ ታቦር፣ ሻደይ በዋግ ኽምራ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በሰሜን ወሎ፣ የከሴ አጨዳ እና እንግጫ ነቀላ በዓላትን በምሥራቅ ጎጃም፣ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራሉ ብለዋል፡፡ በዓላቱ በየአካባቢው ከተከበሩ በኋላ የማጠቃለያ ዝግጅት እንደ ክልል በባሕር ዳር ከተማ የማጠቃለያ ክብረ በዓል እንደሚኖር ገልጸዋል፡፡
እነዚህ በዓላት በየአካባቢዎች በድምቀት እንዲከበሩ ከሐምሌ አንድ ጀምሮ ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዓላቱን በድምቀት ለማክበር በቢሮው የተቀናጀ የግብዓት እና ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡በዓላቱ በድምቀት እንዲከበሩ በማስተባበር የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ሚናውን ይወጣል ያሉት ኀላፊው የክልሉ ሕዝብ፣ በየደረጃው ያለው የመንግሥት መዋቅር በዓላቱ በድምቀት እንዲከበሩ እና ለበዓሉ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ እንግዶችን በማስተናገድ የተለመደ እንግዳ ተቀባይነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን