
ደብረ ማርቆስ: ነሐሴ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር “ጽዱ ኢትዮጵያን ባሕል እናድርግ” በሚል መሪ መልዕክት የጽዳት ዘመቻ ተካሂዷል። የአካባቢ ጽዳት እና ውበት ጽዱ አካባቢን በመፍጠር እና ጤናማ ኅብረተሰብን ለመገንባት አስተዋጽኦው የጎላ ነው።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር አካባቢ ጥበቃ ጽዳት እና ውበት አረንጓዴ ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቸርነት ዓለማየሁ የጽዳት ዘመቻው የመተጋገዝ ልምድን በማዳበር አካባቢን ከብክለት ለመጠበቅ እና የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ታስቦ የተካሄደ መኾኑን ተናግረዋል።
ተጠሪ ጽሕፈት ቤቱ አቅሙን በማሳደግ የከተማዋን ጽዳት እና ውበት ለመጠበቅ ጥረት እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። ኅብረተሰቡ የግሉን እና የአካባቢውን ጽዳት በመጠበቅ የፕላስቲክ ብክለትን ለመከላከል የድርሻቸውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
የጽዳት ዘመቻው የክረምት በጎ ፈቃድ አካል መኾኑን የገለጹት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ “የአካባቢ ጽዳትን መጠበቅ የዘወትር የሥራ ባሕላችን ሊኾን ይገባዋል” ነው ያሉት። በቅንነት አብሮ በመሥራት እና ለሠላም ዘብ በመቆም ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር መሥራት አለብን ብለዋል።
የአካባቢ ጽዳት ከዘመቻ ሥራ ወጥቶ ባሕል መኾን አለበት ያሉት ደግሞ በጽዳት ሥራው የተሳተፉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ናቸው። የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን በማዘመን ጽዱ ከተማ ለመፍጠር በጋራ መሥራት አለብንም ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን