
ባሕር ዳር: ነሐሴ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም ጤና ድርጅት ባለፉት 40 ዓመታት የእናቶችን እና ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ ቆይቷል። በተሠራው ሥራም የእናቶች ሞት 40 በመቶ፤ የሕጻናትን ሞት ደግሞ 59 በመቶ መቀነስ መቻሉን መረጃዎች ያሳያሉ።
ይሁን እንጅ ችግሩ በአንዳንድ ሀገራት አሁንም ሥር የሰደደ ኾኗል። ኖርዌይ ምንም ዓይነት የእናቶች ሞት ያልተመዘገበባት ብቸኛዋ ሀገር ስትኾን ጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን ደግሞ ከ100 ሺህ እናቶች ውስጥ ከ1 ሺህ 200 በላይ የሚኾኑት እናቶች ሕይዎታቸውን የሚያጡባት ሀገረ ኾና ተቀምጣለች።
በኢትዮጵያ ለእናቶች ጤና የተሰጠው ትኩረት እና የእናቶች በጤና ተቋማት ውስጥ ያላቸው የክትትል ባሕል ምን እንደሚመስል ለማየት በደቡብ ጎንደር ዞን ስማዳ ወረዳ ወገዳ ከተማ ነዋሪ የኾኑትን ትርንጎ ሙስጦፋ ተሞክሮ እንሳያችሁ። ወይዘሮ ትርንጎ ከዚህ በፊት በወረዳው ገጠራማ አካባቢ ይኖሩ በነበሩበት ወቅት ከቅድመ ወሊድ ጀምሮ እስከ ድኅረ ወሊድ በጤና ተቋማት ክትትል የማድረግ ልምድ ያላቸው እንደኾኑ ተናግረዋል። በባለሙያዎች በሚደረግላቸው ድጋፍ እና ክትትልም ጤናማ ልጆችን መውለድ መቻላቸውን ገልጸዋል።
ይሁን እንጅ አሁን ላይ ባለው የሰላም ሁኔታበጤና ተቋማት ክትትል ለማድረግ በመቸገራቸው መኖሪያቸውን በወገዳ ከተማ አድርገው በጤና ባለሙያዎች ድጋፍ በሰላም መውለድ ችለዋል።ወይዘሮ ትርንጎ እንዳሉት በጤና ተቋማት ክትትል በማድረጋቸው ከእርግዝና ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ቀድሞ በመለየት ሕክምና እንዲያገኙ አድርጓቸዋል። የአመጋገብ ሁኔታን እንዴት ማስተካከል እንደሚገባ፣ በቅድመ ወሊድ፣ በእርግዝና እና በድኅረ ወሊድ ወቅት መደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ ትምህርት ማግኘታቸውንም ነግረውናል።
ለእናቶች በጤና ተቋማት የሚደረገው ክትትል መሻሻሎች ቢኖሩም ከሰላሙ ጋር ተያይዞ በቤት ውስጥ መውለድን ምርጫ ማድረጋቸውን ትዝብታቸውን አጋርተውናል።እናቶችም የራሳቸውን እና የልጃቸው ጤና የተጠበቀ እንዲኾን ያልተቋረጠ የባለሙያ ክትትል ሊያደርጉ እንደሚገባም መክረዋል። አባዎራዎችም አቅም በፈቀደ መንገድ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት እናቶች ላይ በሠራችው ሥራ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2000 ከሚወልዱ 100 ሺህ እናቶች ውስጥ ይሞቱ የነበረውን 1 ሺህ 30 እናቶች በ2019 ወደ 267 በመቀነስ ውጤታማ ከኾኑ ሀገራት መካከል አንዷ መኾኗን ዋና ሚድዋይፍ ባለሙያ እና ጀማሪ የኅብረተሰብ ጤና ስፔሻሊስቱ ፈንታሁን ፈቃዴ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ግቡን ለማሳካት ከቅድመ ወሊድ፣ ከወሊድ እና ከወሊድ በኋላም ከሚሠሩ ሥራዎች ባለፈ እናቶች እቅድ ላይ ተመሥርተው እና የተሟላ ጤና ላይ ኾነው እንዲወልዱ ቅድመ እርግዝና ላይ ትኩረት ሠጥቶ መሥራት ይገባል ብለዋል።በኢትዮጵያ በቅድመ እርግዝና ወቅት ለእናቶች ጤና ትኩረት አለመስጠት እስከ 94 በመቶ ላልታቀደ እርግዝና ምክንያት ሊኾን እንደሚችልም ገልጸዋል።
በዓለም በዓመት 220 ሚሊዮን፤ በኢትዮጵያ ደግሞ እስከ 5 ሚሊዮን የሚኾን ያልታቀደ እርግዝና እንደሚፈጠር ያነሱት ባለሙያው ከዚህ ውስጥ በዓለም የሚወልዱት 134 ሚሊዮኑ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ 4 ሚሊዮኑ መኾናቸውን አንስተዋል። ሌላው ባልታቀደ እርግዝና ሳቢያ ጽንሱ እንደሚቋረጥ ማሳያ መኾኑን ነው የተናገሩት።
ከቅድመ እርግዝና በፊት ጤናቸውን ሳያውቁ ያረገዙ ሴቶች መውለድ ቢችሉ እንኳ ከእርግዝና በኋላም በሚያጋጥም የተወሳሰበ የጤና ችግር ሕይዎታቸው እንዲያልፍ ያደርጋል ነው ያሉት። መትረፍ ከቻሉም ለመካንነት፣ ለሥነ ልቦና እና ሌሎች አካላዊ ችግሮች ጭምር ሊጋለጡ እንደሚችሉ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን