
ደሴ፡ ነሐሴ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ይህ የክረምት ወቅት ትምህርት ቤቶች ለ2018 የትምህርት ዘመን የተለያዬ ዝግጅት የሚያደርጉበት ወቅት ነው። በደሴ ከተማ የሚገኙት የካራጉቱና የሆጤ አጠቃላይ 2ኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በቀጣይ ዓመት ለመማር ማስተማር ዝግጁ የሚኾኑ የመማሪያ ክፍሎች በመጠናቀቅ ላይ መኾናቸውን የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህራን ለአሚኮ ተናግረዋል።
የካራጉቱ አንደኛ እና መካከለኛ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ወርቁ መሐመድ በ2017 ዓ.ም ከቅድመ አንደኛ ደረጃ 435 ተማሪዎች መመረቃቸውን ጠቁመዋል፡፡ ተማሪዎች በአንድ የመማሪያ ክፍል ከስልሳ በላይ ተማሪዎች እንዲማሩ መደረጋቸውን ገልጸው በቀጣይ የትምህርት ዘመን የተማሪ ክፍል ጥምርታን ለማስተካከል ሥራ መሠራቱን ነው የተናገሩት፡፡
የሆጤ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር ከተማው አንዳርጌ በትምህርት ሚኒስቴር እገዛ ደረጃውን የጠበቀ 12 ክፍሎችን የያዘ ሕንጻ መገንባቱን ጠቁመዋል፡፡ ክፍሎቹ በ2018 ዓ.ም መማር ማስተማር እንዲጀመርባቸው የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም ነው የገለጹት።
አሁንም በትምህርት ቤቱ ከደረጃ በታች ያሉ የመማሪያ ክፍሎች ያሉ በመኾኑ እነዚህን ክፍሎች ደረጃቸውን ወደጠበቁ ክፍሎች እንዲቀየሩ መሥራት እንደሚገባ ነው ያብራሩት። በክረምት በጎ ፍቃድ ትምህርት ቤቶችን ከማደስ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ፍቅር አበበ ገልጸዋል።
ከኅብረተሰቡ፣ ከመንግሥት እና ከተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር 44 የመማሪያ ክፍሎች ተጠናቅቀው በቀጣይ ለመማር ማስተማር ዝግጁ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ኀላፊው አንስተዋል። ሌላኛው በክረምት በጎ ፍቃድ ከተሠሩ ሥራዎች መካከል አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የመማሪያ ደብተር የማሠባሠብ ሥራ ሲኾን እስካሁንም ከ3ሺህ በላይ ደርዘን ደብተር ማሠባሠብ ተችሏል ብለዋል መምሪያ ኀላፊው።
የትምህርት ሥራ ከፍተኛ የገንዘብ እና አቅም የሚጠይቅ መኾኑን ያነሱት መምሪያ ኀላፊው በቀጣይ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እና የመማሪያ ቁሳቁሶችን ለማሟላት በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ሰልሀዲን ሰይድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!