በዘመናዊ ቴክኖሎጅ ታግዞ የሚገነባቸው ሕንጻዎች ተመራጭ እየኾኑ መኾናቸውን ዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

13
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ዘመናዊ ቴክኖሎጅን በመጠቀም በተለያዩ ቦታዎች ሕንጻዎችን በፍጥነት እና በጥራት እየገነባ መኾኑን አስታውቋል። ኮርፖሬሽኑ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ በተገጣጣሚ ቴክኒዎሎጅዎች የተለያዩ ሕንጻዎችን የግንባታ እና የጥገና ሥራ እየሠራ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ በተገጣጣሚ ቴክኖሎጅ የተገነባውን የልህቀት ዲዛይን እና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን ግንባታን፣ የግብርና ቢሮ ባለሁለት ወለል ሕንጻ እና የጤና ቢሮ ሕንጻ እድሳት አስጎብኝቷል።
በጉብኝቱ ወቅት በሕንጻ ግንባታው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ባለሙያዎች ሥለ ቴክኖሎጅዎቹ እና ሥለ ሥራዎቹ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ጉብኝት ከተደረገባቸው የተጠናቀቁ ሕንጻዎች መካከል የልህቀት ዲዛይን እና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን የቪ እይ ፒ ካፌ ይገኝበታል፡፡ ካፌው በአጭር ጊዜ፣ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እና በቀላል ወጭ መጠናቀቁን የተናገሩት የልህቀት የቤተ ውበት ግንባታ ፕሮጀክት አስተባባሪ መስፍን ከበደ ናቸው፡፡
ኮርፖሬሽኑ ሌሎች ግንባታዎችንም በዘመን ኮንስትራክሽን የሸኔል ሆም ተገጣጣሚ ቴክኖሎጅ ግንባታዎችን ያስገነባ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
አስተባባሪው በተመጣጣኝ ወጭ ጥራት ያለው ሕንጻ ባጭር ጊዜ ሠርቶ ማስረከብ መቻሉ ዘመን ኮንስትራክሽንን እንዲመርጡ እንዳደረጋቸው እና ሠርተው ባስረከቧቸው ግንባታዎችም ደስተኞች መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል የግብርና ቢሮ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ስለሽ ሙሉነህ ለቢሮው እየተገነባ ያለው ተጨማሪ ባለሁለት ወለል ሕንጻ ጊዜ ቆጣቢ በኾነ መንገድ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ እና በጥራት የሚከናወን በመኾኑ ዘመንን ተመራጭ እንዳደረገው ነው የተገለጹት። እየተሠራ ባለው የሥራ ጥራት እና የጊዜ አጠቃቀማቸውም ደስተኞች መኾናቸውንም ተናግረዋል።
ዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ዘመናዊ ቴክኖሎጅን በመጠቀም በተለያዩ ቦታዎች ሕንጻዎችን በፍጥነት እና በጥራት እየገነባ ነው፡፡ ይህ ቴክኖሎጅ የጣሊያን እና የጀርመን ቴክኖሎጅ ሲኾን ሸነል ቴክኖሎጅ በመባልም ይታወቃል፡፡ በዚህ ዓመት የተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን ሕንጻ እና የግለሰብ ቤቶችን ጥራታቸውን በጠበቀ መንገድ በቴክኖሎጅ ታግዘው እየገነቡ እንደሚገኙ የዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ታደሰ ግርማ ተናግረዋል፡፡
ሸነል ሆም ቴክኖሎጅ እስከ ዛሬ ከሚጠቀሙባቸው ቴክኖሎጅዎች የላቀ ቴክኖሎጅ ነው ያሉት ዋና ሥራ አሥፈጻሚው ግንባታው አጭር ጊዜ የሚወስድ፣ ወጭ ቆጣቢ፣ በተለዋዋጭ የአየር ንብረት ወቅት ተለዋዋጭነት የሌለው፣ ለእሳት አደጋ በቀላሉ የማይጋለጥ፣ ድምጾችን ወደ ውስጥ የማያስገባ እና ከውስጥ ወደ ውጭም የማያስወጣ መኾኑንም አብራርተዋል፡፡
በተለይ በጊዜ እና በዋጋ ተቀባይነት አለው ነው ያሉት፡፡ በሸንል ሆም ቴክኖሎጅ የተገነባ ሕንጻ በጥራት እና በጥንካሬ ሲታይ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃውን አሟልቶ የሚገነባ ሕንጻ መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡ ሕንጻውም ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስበት ለ90 ዓመታት መቆየት እንደሚችልም ተናግረዋል።
የሸነል ሆም ቴክኖሎጅ የሙያ ክህሎትን እና ቴክኖሎጅን የሚጠይቅ ነው ያሉት ሥራ አስፈጻሚው ሥልጠና በመስጠት ለተለያዩ ወጣቶች የሥራ ዕድል እየፈጠሩ መኾኑንም አብራርተዋል፡፡ የዘመን ኮንስትራክሽን ዓላማ ዘመን ተሸጋሪ ግንባታ መገንባት በመኾኑ እስካሁን በሠራቸው ሥራዎች ደንበኞቹ እንደሚመርጡት እና ደንበኞች እንደኾኗቸውም ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበሸማች ማኅበራት እና ዩኒየኖች በኩል መሠረታዊ የፍጆታ ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ተችሏል፡፡
Next articleበተያዘው ክረምት የመማሪያ ክፍሎችን ግንባታ በማጠናቀቅ ለቀጣይ መማር ማስተማር ሥራ እየተዘጋጁ ነው።