
ደብረማርቆስ፡ ነሐሴ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ)
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ በዞኑ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እና በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን ለመደገፍ በሸማች ማኅበራት በኩል መሠረታዊ የፍጆታ ምርትን በማቅረብ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡ለመንግሥት ሠራተኞች እና በዝቅተኛ ገቢ ለሚኖሩ ዜጎች የፍጆታ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ሲቀርብ መቆየቱን ገልጸዋል። በቀጣይም ገበያውን ለማረጋጋት እና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሠራል ነው ያሉት፡፡
ዓለም አቀፍ ተጽዕኖው፣ በገበያ ውስጥ የሦስተኛ ወገን (የደላላው) መበራከት፣ አምራች እና ሸማችን ለማገናኘት የመሠረተ ልማት ችግር እና ሕግን ባልተከተለ መንገድ የተሰማሩ ነጋዴዎች ለገበያ ዋጋ መናር መንስኤዎች እንደኾኑም አብራርተዋል፡፡አለመረጋጋቱን መነሻ በማድረግ ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ በተሰማሩ አካላትም ቁጥጥር እና ክትትል እየተደረገ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
የምሥራቅ ጎጃም ዞን የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፋፊያ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ታረቀኝ ጀንበሬ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት 56 ሚሊዮን ተዘዋዋሪ ገንዘብን በመጠቀም ከ6ሺህ በላይ ኩንታል መሠረታዊ የፍጆታ ምርት በሸማች ማኅበራት ቀርቧል ብለዋል።ተጠሪ ጽሕፈት ቤቱ 7ሺህ 300 ኩንታል ጤፍ እና 500 ኩንታል የፊኖ ዱቄት በዞኑ በሚገኙ ዩኒየኖች ግዥ በመፈጸም ለዞን የመንግሥት ሠራተኞች እና በዝቅተኛ ገቢ ለሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለማሰራጨት እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከልም ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር እየተሠራ መኾኑ ተገልጿዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!