
ደሴ: ነሐሴ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ገበያን ለማረጋጋት በንቃት ለተሳተፉ ነጋዴዎች፣ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች፣ አስመጭዎች እና ላኪዎች ዕውቅና ሰጥቷል። የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ” የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መሪ መልዕክት የንግድ ቀንን አክብሯል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድ አሚን የሱፍ የከተማ አሥተዳደሩ ለሚያከናውናቸው የተለያዩ ተግባራት የንግዱ ማኅበረሰብ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው ብለዋል። ገበያን ለማረጋጋት የከተማዋ ነጋዴዎች መልካም ተግባራትን አከናውነዋል ነው ያሉት ።
በሕገ ወጥ መንገድ የሚሠሩ፣ ጊዜው ያለፈበትን ምርት የሚሸጡ እና ምርት በማከማቸት እጥረት እንዲፈጠር እያደረጉ የሚገኙ ነጋዴዎችን እንደማይታገሱም ገልጸዋል። በመድረኩ የተሳተፉ ነጋዴዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ እያቀረቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በከተማው የተለያዩ ዘርፎች ላይ የተሠማሩ ነጋዴዎች እና ኢንዱስትሪዎች የነዳጅ እጥረት፣ የመብራት መቆራረጥ፣ የመንገድ እና የውኃ አቅርቦት ችግር እንዳለባቸው አንስተዋል ። ነጋዴዎች በተሠማሩበት የንግድ መስክ ማኅበረሰቡን በሚገባ በማገልገላቸው ከተማ አሥተዳደሩ ላበረከተላቸው ዕውቅና ምስጋና አቅርበዋል ።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ዮናስ መላኩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ1ሺህ 800 በላይ ነጋዴዎች ያለ ንግድ ፈቃድ ሢሠሩ መገኘታቸውን ጠቁመዋል። ከእነዚህ ውስጥም 1ሺህ 400 የሚኾኑትን ወደ የንግድ መረቡ ማስገባት ተችሏል ብለዋል።
በዓመቱ 16 የንግድ ባዛሮችን በማካሄድ ከ90 ሺህ ኩንታል በላይ የኢንዱስትሪ እና ከ40 ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና ምርቶችን ለነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። ከንግዱ ማኅበረሰብ ለተነሱ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችም ከተማ አሥተዳደሩ በሂደት ምላሽ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል። በመድረኩ በገበያ ማረጋጋት እና በተለያዩ ተግባራት በንቃት ለተሳተፉ ነጋዴዎች፣ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች፣ አስመጭዎች እና ላኪዎች ዕውቅና ተሰጥቷል ።
ዘጋቢ: ከድር አሊ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን