የኮሪያ መንግሥት ለኢትዮጵያ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ።

17
አዲስ አበባ፡ ነሐሴ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኮሪያ መንግሥት ለኢትዮጵያ ለንፁሕ መጠጥ ውኃ እና ለመጀመሪያ ደረጃ ጤና አገልግሎት የሚውል የ1 ነጥብ 37 ቢሊዮን ብር ድጋፍ አስረክቧል።
በድጋፍ ርክክቡ ላይ በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ አቡበከር ካምፖ (ዶ.ር) የኮሪያ ሪፐብሊክ መንግሥት ዓለም አቀፋዊ ድጋፎች በተቀዛቀዙበት ወቀት ለንፁሕ መጠጥ ውኃ እና ለመጀመሪያ ደረጃ ጤና አገልግሎት ድጋፍ ማድረጉ መልካም ነው ብለዋል።የኮሪያ ሪፐብሊክ ባለፉት አምስት ዓመታት ለዩኒሴፍ ፕሮግራሞች ከ17 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጓል።
ዛሬ የተደረገው ድጋፍ በርካታ ሰብዓዊ ቀውሶች በገጠሙበት ወቅት መኾኑ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል። ለድጋፉም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በመርሐግብሩ በኢትዮጵያ የኮሪያ አምባሳደር ጃንግ ካንግ ኮርያ እና ኢትዮጵያ በታሪክ ጥብቅ ተስስር ያላቸው ሀገራት ናቸው፤ “ዛሬ ሀገሬ ያደረገችው ድጋፍ የሁለቱን ሀገራት ትስስር እና ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር ነው” ብለዋል።
ድጋፉ በከፋ ችግር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ሕይዎት ለማሻሻል እና አጋርነትን ለማሳየት የተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። የጤና ሚኒስቴር ተወካይ እስራኤል አታሮ ድጋፉ መንግሥት እያደረገው ላለው የዜጎች ጤና መጠበቅ ትልቅ አስተወጽኦ አለው ነው ያሉት። በተለይም በተለያዩ ችግሮች ጉዳት የደረሰባቸውን ሕጻናት እና እናቶች ሞት ለመቀነስ ለሚደረገው ጥረት ድጋፉ አስተዋጽኦው ጉልህ ነው ብለዋል።
የውኃ እና ኢነርጅ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋዉ ዴንጋሞ (ዶ.ር) የኮርያ ሪፐብሊክ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የሁለቱን ሀገራት የዘመናት ጥብቅ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ያደረገ እንደኾነ ጠቁመዋል። መንግሥት እያካሄዳቸው ላሉ የንፁሕ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት ሚናው የላቀ ነውም ብለዋል። ድጋፉ በስድስት ክልሎች የሚገኙ ከ364ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሐመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋ
Previous articleአስበው የሠሩት ብርቱው ሰው
Next articleየኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ገበያን ለማረጋጋት በንቃት ለተሳተፉ አካላት ዕውቅና ሰጠ።