አስበው የሠሩት ብርቱው ሰው

17
ባሕር ዳር: ነሐሴ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በቀደምት ሥልጣኔዋ እና ታሪኳ ትታወቃለች። የተፈጥሮ ሀብቷ፣ ተስማሚ የአየር ንብረቷ እና ሌሎች የሚዘረዘሩ ሀብቶቿ ናቸው። በርዝመቱ እና ፖለቲካዊ ታሪኩ የሚታወቀው የዓባይ ወንዝ መመንጫም ናት።ይህ ሁሉ ማንነቷ ግን ከድህነት ሳያወጣት ኖሯል። የውኃ ማማ እና የሰፊ መሬት ባለቤትነቷንም ሳትጠቀምበት ኖራለች። ዓባይም ለቁጭት የሥነ ቃል ምንጭ ከመኾን ያለፈ አልጠቀማትም ነበር።
ለዘመናት የባዕድ ሲሳይ ኾኖ የኖረው ዓባይ የኤሌክትሪክ ኀይል ሊያመነጭ፣ የእናቶችን ስቃይ ሊያስቀር እና ኢትዮጵያን በኢንዱስትሪ ሊያንበሸብሽ መጋቢት 24/2003 ዓ.ም ብሥራት ተሰማ። መላ ኢትዮጵያውያን ርቀት፣ ብሔር፣ ፖለቲካ እና የሀብት ልዩነት ሳያግዳቸው በአንድነት ተነሱ። የፖለቲካ ፓርቲዎች በዓባይ ላይ ተስማሙ። አዋጁ እንደ ዓድዋ ሁሉ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ያነሳሳ ኾነ።
የቀን ሠራተኞች ገንዘብ ለማዋጣት በአደባባይ ቃል ገቡ። እናቶች ከመቀነታቸው፣ ሽማግሌዎች ከኪሳቸው፣ ሕጻናት ከወላጆቻቸው፣ እየተቀበሉ ለገሱ። ከውጪ የሚመጣን ማንኛውም ጫና ለመቋቋም እስከ ደም ጠብታ እንደሚከፍሉ ተማማሉ። ዜናው፣ ሙዚቃው፣ ውይይቱ፣ መፈክሩ ሁሉም ነገሮች ዓባይ ላይ አተኮሩ።
አቶ አስማረ ኀይሌ በባሕር ዳር ከተማ አጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ አየር ጤና ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። የዓባይ ግድብ ሲጀመር በብአዴን ጽሕፈት ቤት የግቢ ውበት ባለሙያ ነበሩ። የዓባይ መገደብ ሲታወጅ ደስታቸው ከልክ በላይ ኾነ። ዓባይን በመገደብ ድህነትን ማሸነፍን ይገነዘባሉና።
በወቅቱ የአቶ አስማረ የተጣራ ደመወዝ 650 ብር ነበር። ትዳር እና ልጆችም አሏቸው። ነገር ግን አቅም የለኝም አላሉም። አርዓያ ለመኾን ‘ከአቅማቸው በላይ’ ቦንድ በመግዛት ለመደገፍ ቃል ገቡ እንጂ።
ሕዝቡ በወኔ እና በጉጉት ቢሳተፍም ሥራው ሳይጠናቀቅ አምስት ዓመታት ሞላው፡፡ ጉርምርምታ ተፈጠረ። አቶ አስማረ ግን የጀመርሁትን ሳልጨርስ ለማን እተወዋለሁ? በማለት የቦንድ ግዢያቸውን ቀጠሉ፡፡ የሕዳሴ ግድቡን ግንባታ ሲጎበኙም የገዙትን ቦንድ በመረከብ ከሠራተኞች ጋር አክብረዋል። በዚያ በረሃ ላይ 24 ሰዓታት የሚሠሩ ጀግኖችንም አበረታተዋል።
ጉብኝታቸው የበለጠ ስላነሳሳቸው የቦንድ ግዥውን አስቀጠሉ፡፡ ”ብሞት እንኳ የቦንድ ግዡ ከጡረታዬ ላይ እንዲቀጥል አደራ…” ማለታቸውን አቶ አስማረ ገልጸዋል፡፡ ባለቤታቸው አበጀህ! እንኳን አደረግኸው በማለት እንደሚያበረታቷቸው ነው የገለጹት። የአቶ አስማረ ባልደረቦች በሙሉ እስከ አምስት ዓመታት ያለማቋረጥ ከፈሉ። እየቆየ ቁጥራቸው ቢቀንስም አቶ አስማረ ግን እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ቀጠሉ። እስከ 70 ሺህ ብር የሚደርስ ቦንድም ገዝተዋል፡፡
በ2010 ዓ.ም የለውጥ ዋዜማ አካባቢ የሕዳሴ ግድቡ ግንባታ ባጋጠመው የመዘግየት እና መሰል ችግሮች ላይም ተስፋ አለመቁረጣቸውን ነው የገለጹት። ፕሮጀክቱ ገና ሲጀመርም በታሰበው ልክ ላይሄድ እንደሚችል እገምት ነበር ያሉት አቶ አስማረ ችግር ቢገጥምም ወድቀን ተነስተን እንደምንጨርሰው ግን እምነቱ ነበረኝ ብለዋል፡፡
አቶ አስማረ የኢትዮጵያውያን ጽናት እና ትብብር፣ በዓለም አደባባይ የእነ ኢንጅነር ስለሺ በቀለ (ዶ.ር) ሙግት፣ የዓለምን ሕዝብ አሳምነን እና የግብጽን የዲፕሎማሲ ጫና ተቋቁመን ግድባችንን እንድናጠናቅቅ አስችሎናል ነው ያሉት። በቀጣይም ለግድቡ ደኅንነት የበኩላቸውን ለማበርከት ዝግጁ መኾናቸው ገልጸዋል፡፡
ግድቡን በውጤታማነት ለመጠቀም ብስለት በተሞላበት አካሄድ መመልከትን ይጠይቃል ብለዋል። ግብጽ በግድቡ ዙሪያ የምታነሳውን ጥያቄ መንግሥት ለሚያደርገው ዲፕሎማሲያዊ ትግል ሕዝቡ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ነው የሚሉት። ምሁራን እና የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች ኅብረተሰቡን ማንቃት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
የሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለመጀመር ያስችላል፡፡ በአንድነት የመሥራትን ጠቀሜታ ያሳያል። ግድቡ የመጀመሪያችን እንጂ የመጨረሻችን እንደማይኾን እገነዘባለሁ። ስለዚህ ሌሎች ፕሮጀክቶችንም ለመገንባት መነሣሣት አለብን ብለዋል። እንደ ዓድዋ ድል ሁሉ የሕዳሴ ግድባችን ሌላኛው ታሪካችን ነው። ሦስተኛም መድገም አለብን ብለዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ በዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሀገር በቀል ችግኞች ለባሕልና ቱሪዝም ዘርፍ ትርጉማቸው የተለየ ነው።
Next articleየኮሪያ መንግሥት ለኢትዮጵያ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ።