
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ፣ የአሚኮ፣ የአማራ የስቴት ዩኒቨርሲቲ እና የአማራ ክልል ምክር ቤት ሠራተኞች እና መሪዎች በባሕር ዳር ከተማ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
የጉብኝቱ ተሳታፊ የኾኑት የሽዋስ አማረ
በከተማ አሥተዳደሩ የተሠሩት ሥራዎች የነበረውን የከተማዋን ውበት ይበልጥ የሚያደምቅ ነው ያሉት። የከተማውን ልማት ለማስቀጠል ደግሞ የማኅበረሰቡ ተሳትፎን ማጠናከር እና ሰላሙን ማስጠበቅ ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
ሌሎች አካባቢዎችም ሰላማቸውን በማስጠበቅ ልማት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው መክረዋል።
ሌላኛዋ የጉብኝቱ ተሳታፊ ማስተዋል አለምነው በከተማ አሥተዳደሩ የተሠሩ የልማት ሥራዎች የባሕር ዳርን ውበት ይበልጥ የሚያጎላ መኾኑን ገልጸዋል። ተሞክሮወን ወደ ሌሎች ከተሞች ማስፋት ይገባል ብለዋል። ማኅበረሰቡም የተሠሩ የልማት ሥራዎችን መጠበቅ እንዳለበትም ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ ጉብኝቱ በክልሉ የሚገኙ ሠራተኞች የተሠሩ የልማት ሥራዎችን ተረድተው ለሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችም እንዲያስተዋውቁ እና ለቱሪዝም ልማቱም አጋር እንዲኾኑ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ምክትል ከንቲባው የተሠሩ የልማት ሥራዎች ከተማዋ ያላትን የተፈጥሮ ውበት ይበልጥ የገለጠ ነው፤ የጎብኝዎችን ቆይታ በማራዘም የማኅበረሰቡን ምጣኔ ሃብት የሚያሳድግም ነው ሲሉ ተናግረዋል። ማኅበረሰቡም የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ የተጀመረውን ልማት እንዲደግፍ ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) የክልሉ መንግሥት ሠራተኞች የ25 ዓመት አሻጋሪ እቅድ እና ከ2018 በጀት ዓመት እቅድ ውይይት በኋላ በከተማ አሥተዳደሩ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን እንዲጎበኙ ተደርጓል ብለዋል።
በጎብኝቱ በአብዛኛው የተሳተፉት የሚዲያ ባለሙያዎች እንደመኾናቸው የተሠራውን የልማት ሥራ አውቀው የገጽታ ግንባታ ሥራ እንዲሠሩ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ የተሠሩ የልማት ሥራዎች ለሌሎች ከተሞችም ምሳሌ የሚኾኑ ናቸው ብለዋል። የቱሪዝሙን ዘርፍንም የሚያሳደግ በመኾኑ ማኅበረሰቡ የተጀመረው ልማት እውን እንዲኾን ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!