
ባሕር ዳር: ሐምሌ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከዞን፣ ከከተማ አሥተዳደር እና ከወረዳ ለተውጣጡ ሴት የሥራ ኅላፊዎች እና እጩ ሴት መሪዎች በባሕር ዳር ከተማ ሲሰጠው የነበረው ሥልጠና ተጠናቋል።
ሥልጠናው የሴቶችን የመሪነት ብቃት ማዳበር፣ የቀውስ ጊዜ መሪነት እና የመሪነት ሚናን ማሳደግ ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር።
ሥልጠናውን ሲከታተሉ ከነበሩ ሴት መሪዎች ውስጥ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጓንጓ ወረዳ ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እቴነሽ አባተ ይገኙበታል።
ለአምስት ቀናት የተሰጣቸው ሥልጠና ከዚህ በፊት ከነበራቸው ልምድ ላይ ተጨማሪ አቅም የፈጠረላቸው መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ለቀጣይ ሥራም መነሳሳትን እና ቁርጠኝነትን የፈጠረ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ሴቶች ኀላፊነት ሲይዙ ማድረግ ያለባቸውን እና በቀውስ ወቅት በመሪነት ሚናቸው መፍትሔ አመላካች መኾን እንደሚችሉ የተረዱበት ሥልጠና መኾኑን ነው የገለጹት። ሴቶች በርካታ ኀላፊነቶችን ተሸክመው የመምራት ብቃት ያላቸው ናቸው ብለዋል።
ሴቶች በማኅበረሱቡ ዘንድ ተቀባይነት አላቸው ያሉት ወይዘሮ እቴነሽ ከሥልጠናው ያገኙትን ልምድ እና ግንዛቤ ለሌሎች ሴት መሪዎች ለማካፈል ዝግጁ መኾናቸውንም አብራርተዋል፡፡ አቅማቸውን በማጎልበት ወደ መሪነት እንዲመጡ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ሌላኛዋ የሥልጠናው ተሳታፊ የዳንግላ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ክንፍ ኀላፊ እመቤት ፈንቴ በሥልጠና ቆይታቸው ከጠበቁት በላይ አቅም የሚኾን ግንዛቤ እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡ ወቅቱ አስቸጋሪ ከመኾኑ ጋር በተያያዘ ሥልጠናው ይህንን ችግር ሴት መሪዎች እንዴት ማለፍ እንደሚችሉ የሚያሳይ እና መፍትሔ አመላካች ነው ብለዋል።
ሴት መሪዎች በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም እጦት ለማረጋጋት ከፍተኛ ድርሻ እንዲወጡ የሚያስችል እንደኾነም ነው የተናገሩት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የመሬት መምሪያ ኀላፊ መልካምሥራ ካሳው ሥልጠናው ወቅቱን የዋጀ እና ለሴት መሪዎች አስፈላጊ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ሴት ትችላለች የሚለውን አስተሳሰብ በማኅበረሰቡ ዘንድ እንዲጎለብት መሥራት እንድንችል እና ቁርጠኝነትን የፈጠረ ሥልጠና መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥርዓተ ጾታ እኩልነት የአማራ ክልል ማሥተባበሪያ ፕሮግራም ኦፊሠር ደሳለው አለኸኝ ሥልጠናው ሴቶች የራስ መተማመን እንዲያጎለብቱ፣ የመሪነት ተሳትፏቸው እንዲያድግ፣ በፖለቲካውም ውክልና እንዲኖራቸው የአቅም መገንቢያ ሥልጠና መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ራስን ማየት ላይ እና ውቅረ ልቦና ላይ እኔ እችላለሁ የሚል መንፈስ እንዲያዳብሩ ያግዛል ነው ያሉት። እኔ አልችልም፣ አይኾንልኝም ከሚል አስተሳሰብ ወጥተው ማድረግ እችላለሁ የሚል አስተሳሰብ እንዲይዙ ለማድረግ ሥልጠናው ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
መሪነት ምን ማለት እንደኾነም ግንዛቤ ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡-ሰለሞን ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን