ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለባለውለታዎች እውቅና ሰጠ።

22

ባሕር ዳር: ሐምሌ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ እና የማስተማሪያ ሆስፒታሉ 100ኛ ዓመት ምሥረታ ማጠቃለያ መርሐ ግብር እያካሄደ ነው። በመርሐ ግብሩ ለተቋሙ እና ለሀገር አሥተዋጽኦ ላበረከቱ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ሕንጻዎች በስማቸው ተሰይሞላቸዋል። እውቅናው ግለሰቦቹ ካበረከቱት አስተዋጽኦ መጭው ትውልድ እንዲማርበት ለማድረግ ያግዛልም ተብሏል።

ስያሜ ከተሰጣቸው ታዋቂ ሰዎች ውስጥ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ይገኙበታል። ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ የጎንደርን ጤና አጠባበቅ ኮሌጅን ያቋቋሙ፣ የማራኪ ዩኒቨርሲቲን መሠረት ያስቀመጡ የሀገር መሪ ናቸው ተብሏል በዕለቱ።

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት እና ጤና አጠባበቅ እንዲስፋፋ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ዩኒቨርሲቲው በማራኪ ግቢ የሚገኘው ሁለገብ አዳራሽ በስማቸው ተሰይሟል።

ሌላኛው በዩኒቨርሲቲው ስያሜ የተሠጣቸው በርናርድ አንደርሰን (ዶ.ር) ናቸው። ዶክተር በርናንድ አንደርሰን ታዋቂ የቀዶ ሕክምና ሐኪም ናቸው። በጎንደር ሕክምና ኮሌጅ ለ10 ዓመታት በሕክምና ሙያ አገልግለዋል። የድኅረ ምረቃ ተማሪዎችን በማስተባበር እና በማማከር ከፍተኛ ሥራ ሠርተዋል። ልምዳቸውን ለባለሙያዎች ጭምር በማካፈል አቅም እንደኾኑ በዕለቱ ተገልጿል።

ሌላኛው ስያሜ የተሰጣቸው ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ ናቸው። ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው በርካታ ምሁራንን ያፈሩ፣ የመምህራንን መኖሪያ ቤት ችግር እንዲፈታ ያደረጉ እና በዩኒቨርሲቲው የማስፋፊያ ግንባታዎችን በማስገንባት የነበረውን ችግር እንዲቃለል አድርገዋል።

ከ60 በላይ የምርምር ሥራዎችንም በመሥራት ለሀገር አበርክተዋል። አሁን ላይ አፍሪካውያንን ያሳተፈ የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን መርሐ ግብር ያስጀመሩ እና እያማከሩ የሚገኙ የሀገር ባለውለታ ናቸው።

ደሳለኝ መንገሻ (ዶ.ር) የዩኒቨርሲቲውን የድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር በማስፋፋት፣ የ20 ዓመት ማስተር ፕላኑን በማዘጋጀት እና የስቲም ማዕከሉን ወደ ተቋም እንዲያድግ ያደረጉ ናቸው። የአካዳሚክ መርሐ ግብሮችን እና የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በማስፋፋት ተቋማዊ አቅምን የማጠናከር ሥራ ሠርተዋል ተብሏል።

ሌላው ባለውለታ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ናቸው። በዓለም አቀፍ የፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ሥራ ሠርተዋል። በተለይም የተጨቆኑ እና የተገለሉ ሰዎች ላይ ያማከሉ ሥራዎችን በመሥራት ለነጻነት እና ለፍትሕ የቆሙ ባለውለታ ናቸው። ከኢትዮጵያዊነት ባለፈ ፓንአፍሪካኒዝምን በማቀንቀንም የሚታወቁ ናቸው።

በ1963 ዓ.ም መሬታቸውን ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ በፈቃደኝነት ለሰጡ 59 አርሶ አደሮችም በዩኒቨርሲቲው ማራኪ ግቢ ታላቅ ሕንጻ ታወር 59 ተብሎ ተሰይሟል።

ሌላኛው እውቅና የተሠጠው ውስብስብ ጉዳዮችን በቀላል መንገድ በማቅረብ ለሚታወቁት ሞጋች ጋዜጠኛ እና ደራሲ ብርሃኑ ዘርሁን ነው። በዘመኑ ፖለቲካዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ፤ በአጫጭር እና ረጅም ልብ ወለዶችን በተከታታይ በማቅረብ የታወቁ ባለውለታ ናቸው።

ከዚህም በተጨማሪ ለፕሮፌሰር ማለደ ማሩ፣ ለዶክተር ያሬድ አሰፋ፣ ለዶክተር ነብዩ መስፍን፣ ለቤተር ራይዝሽ፣ ለፕሮፌሰር ደኒዝ ዲ ካርልሰን፣ ለፕሮፌሰር ያሬድ ወንድምኩን እና ለሎሬት ሙላቱ አስታጥቄ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ሕንጻዎች በስማቸው እንዲሰየም ተደርጓል።

በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለነበሩት ታላቁ ፈላስፋ ዘረዓ ያዕቆብ፣ በታሪክ ለነጋዴዎች አለቃ ይሰጥ የነበረው”ነጋ አድራስ”፣ ለ33ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሀሪ ትሩማን፣
የ20ኛው ክፍለ ዘመን ፈላስፋ እና ገጣሚ ለኾኑት ዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ፣ በብዝኀ ሕይወቱ ለሚታወቀው አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ፣ አልሙናይ እና ዳኘ እንግዳው እውቅና ካገኙት ግለሰቦች እና ድርጅቶች ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው።

ዘጋቢ: ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleአፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ እየወሰደችው ላለው የመፍትሔ እርምጃ 3 ትሪሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል።
Next articleየጎንደር ዩኒቨርሲቲ የገዘፈ እና የላቀ ኾኗል።