አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ እየወሰደችው ላለው የመፍትሔ እርምጃ 3 ትሪሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል።

18

አዲስ አበባ: ሐምሌ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመተባበር ሁለተኛውን የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ከጳጉሜ 03 እስከ ጳጉሜ 05/2017 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ ለማስተናገድ ዝግጅት እያደረገች ትገኛለች። የጉባዔውን ዝግጅት አስመልክቶ የኢፌዴሪ ፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ለመገናኛ ብዙኅን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና የአካባቢ ደኅንነትን ለመጠበቅ የሚያስችል የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሐ ግብር ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች ብለዋል።

በዚህም ተጨባጭ ለውጥ አስመዝግባለች ነው ያሉት። ተግባሩ ለሌሎች ሀገራትም ልምድ እና ተሞክሮ የሚኾን እንደኾነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት እና የኢነርጅ ዘርፉን በታዳሽ ኃይል ለመተካት ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እየገነባች ነው ብለዋል። ለአብነትም የአረንጓዴ አሸራ መርሐ ግብር እና በቅርቡ የሚመረቀው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።

ጉባዔው አፍሪካዊያን በአየር ንብረት ለውጥ የጋራ አቋም የሚይዙበት ሲኾን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ በመፍጠር የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች እንደኾነ ነው የገለጹት። አፍሪካዊያን ለአየር ንብረት ለውጥ እየወሰዱት ያለውን ተጨባጭ የመፍትሔ እርምጃዎች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስተዋወቅ ያለመ ነውም ነው ያሉት።

የአፍሪካዊያን የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እየወሰዱት ያለው ተጨባጭ የመፍትሔ እርምጃዎችም ተገቢ እና ፍትሐዊ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኝ ለማድረግ ሚናው ከፍተኛ እንደኾነም ተናግረዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ ያለውን ተጎጅነት እና ተጠቂነት ለመከላከል አሕጉር አቀፍ የመፍትሔ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ለመፍትሔ እርምጃዎችም ዓለም ዓቀፉ ተቋማት የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውን አንስተዋል።

በጉባዔው ዓለም አቀፍ ተቋማት ለአየር ንብረት ለውጥ ቃል የሚገቡትን የፋይናንስ ድጋፍ በተግባር የሚያሳዩበት እና መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ውሳኔዎች የሚወሰንበት ጉባዔ እንደሚኾን ይጠበቃል ነው ያሉት በመግለጫቸው።

አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ እየወሰደችው ላለው የመፍትሔ እርምጃ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከ3 ትሪሊዮን ዶላር በላይ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት ነው የገለጹት።

በጉባዔው የ45 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችን ጨምሮ 25 ሺህ የሚኾኑ ተሳታፊዎች እንደሚገኙም ተጠቁሟል።

ጉባዔው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሔዎችን ማፋጠን፤ የአፍሪካን የማይበገር እና አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ” በሚል መሪ መልዕክት እንደሚከበርም ተገልጿል።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዕድገት ምስጢሩ አጋር አካላትን ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ መፍጠር መቻሉ ነው፡፡
Next articleጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለባለውለታዎች እውቅና ሰጠ።