የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዕድገት ምስጢሩ አጋር አካላትን ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ መፍጠር መቻሉ ነው፡፡

11

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ እና የማስተማሪያ ሆስፒታሉ 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው። የቀድሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለእርሳቸው እና በመድረኩ ላልተገኙ ብሎም በሕይዎት ለሌሉ ባልደረቦቻቸው ለሰጠው ዕውቅና አመሥግነዋል፡፡

በቀድሞው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ሳይነስ ኮሌጅ በአሁኑ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከዲፕሎማ ተማሪ እስከ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንትነት ብሎም የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ እስከደረሱበት ድረስ ለ38 ዓመታት በተቋሙ መሥራታቸውን ተናግረዋል፡፡

የቀድሞው የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ገጽታ ተማሪ እያሉ ቁጭት እንዳሳደረባቸው ነው የተናገሩት፡፡ በጣሊያን ጊዜ የተሠራው የዩኒቨርሲቲው ገጽታ አለመቀየር እንደተማሪም ኾነ በዩኒቨርሲቲው እንደ መሪ ቁጭት ይፈጥርባቸው እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡

ቁጭቱ እያደገ በመሄድ ለለውጥ አገልግሎ ለዛሬው የዩኒቨርሲቲው ለውጥ መነሻ መኾኑን ነው ያብራሩት፡፡ በዩኒቨርሲቲው የነበረውን የተጨናነቀ የተማሪዎች መማሪያ ክፍል፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁ የተማሪዎች ማደረሪያ እና የአሥተዳደር ሕንጻዎችን ለመቀየር የተሠራው ሥራ እንደማሳያ ማንሳት እንደሚቻል ነው የተናገሩት፡፡

ሕንጻዎቹ በተለያየ ጊዜ ለተለያየ አገልግልሎት ውለው ስለነበር ደረጃቸው ዝቅ ያለ እንደነበር ነው ያስረዱት፡፡

በዩኒቨርሲቲው ለስምንት ዓመት በመሪነት ደረጃ አገልግለው ስለነበር የነበራቸውን ቁጭት ዩኒቨርሲቲው እንዲቀየር እና ገጽታው በሁሉም በኩል እንዲሻሻል ለማድረግ ከሥራ ባልደረቦቻቸው እና ከተቋሙ ሠራተኞች ጋር መሥራታቸውን ነው ያብራሩት፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዕድገት ምስጢሩ ሀገርን ማስተዋወቅ እና አጋር አካላትን ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ድረስ መፍጠር መቻሉ እንደኾነ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲን የበላይ እና መካከለኛ መሪዎችን አቅም ማጎልበትም ዩኒቨርሲቲው የሠራው ትልቁ ሥራው እንደኾነ ነው ያስረዱት፡፡

እነዚህ ሥራዎች እንደ ባሕል ተወስደው መዳበራቸው ዩኒቨርሲቲው የላቀ ደረጃ እንዲደርስ እንዳስቻለው ነው የጠቆሙት፡፡ የውስጥ አቅምን ማሳደጉ እና በመሠረተ ልማት የሠራው ሥራ ውጤት እንዲመጣ እንዳስቻለውም ተናግረዋል፡፡

መምህራን በዩኒቨርሲቲው እንዲቆዩ የተደረገበት ሥራም ውጤት አምጠቷል ነው ያሉት፡፡ የተለያዩ ፌስቲቫል እና የዩኒቨርሲቲውን ገጽታ ለመገንባት የተደረው ጥረትም በበጎ የሚነሳ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

የማስተር ካርድ ፕሮጀክት ወደ ትዮጵያ የመጣው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተወዳድሮ 24 ሚሊዩን ዶላር በማምጣቱ እንደኾነ የተናገሩት ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ ዛሬ ተማሪዎች ወደ ውጭ ተልከው እንዲማሩ ከማድረጉ በተጨማሪ ከጎረቤት ሀገር ከኤርትራ፣ ከጅቡቲ፣ ከሶማሊያ፣ ከሱዳን እና ከኬኒያ ተማሪዎችን በማምጣት በዩኒቨርሲቲው እንዲመረቁ ማድረግ ስለማስቻሉ ነው ያብራሩት፡፡

ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዲያገኝ የተሠራው ሥራም ውጤት የተገኘበት እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቀጣይ እድገቱን ለማስቀጠል ከታች መሪዎችን እያበቃ ማምጣት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡ የጋራ ባሕልን አጠናክሮ መቀጠልም በሰፊው ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ተወዳዳሪ መኾን እና የዩኒቨርሲቲውን የራስ ገዝ ሁኔታ ተረድቶ ከፍተኛ ገቢ ለማምጣት መሥራት የሚጠበቅ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ በመማር ማስተማር፣ በምርምር እና በማኅበተረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ተጽዕኖ በመፍጠር ከሀገር እስከ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ መፍጠር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

መሪዎች ወደፊት ተሳስበው ከሠሩ ውጤት እንደሚያመጡም ነው የተናገሩት፡፡ በዩኒቨርሲቲው ተሳስቦ እና ተናቦ የሚሠራው ሥራ እና ዩኒቨርሲቲው ከከተማዋ ጋር ተጣምሮ እየሠራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ እና የማስተማሪያ ሆስፒታሉ 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ተቋማዊ እና ሀገራዊ ፍሬዎች የታዩበት ነው።
Next articleአፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ እየወሰደችው ላለው የመፍትሔ እርምጃ 3 ትሪሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል።