የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ እና የማስተማሪያ ሆስፒታሉ 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ተቋማዊ እና ሀገራዊ ፍሬዎች የታዩበት ነው።

20

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ እና የማስተማሪያ ሆስፒታሉ 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አሥራት አጸደወይን (ዶ.ር) የጎንደር ዩኒቨርሲቲን 70ኛ እና የማስተማሪያ ሆስፒታሉን ደግሞ 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በድምቀት ተጀምሮ በስኬት ለፍጻሜው መብቃቱን ገልጸዋል።

የምስረታ በዓሉ ከጥር 2017ዓ.ም ጀምሮ ሲከበር መቆየቱን ገልጸዋል። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያ ሆስፒታል ከድህረ ዓድዋ የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ማዕቀፍ ጋር እንደሚገናኝ ተናግረዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያ ሆስፒታል በቸቸላ ለቆንስላ ጽሐፈት ቤት በተገነባው ላይ እንደጀመረ አስታውሰዋል። በ1945 ዓ.ም በደንቢያ አካባቢ የተከሰተው የወባ ወረርሽኝ በጎንደር የጤና ኮሌጅ እንዲቋቋም መነሻ እንደኾነም ተናግረዋል። የቸቸላ ሆስፒታል የኢትዮጵያ ቀደምት የጤና የትምህርት ተቋም እንዲወለድ ምክንያት መኾኑንም ገልጸዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቀደምት ተቋም ኾኖ ሲመሰረት፣ የዓለም አጋር ድርጅቶች እንደተባበሩለት ሁሉ ተቋሙን ለማስቀጠልም የሀገር ውስጥ እና የውጭ ተቋማት ድጋፍ እንዳልተለየው አንስተዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በማኅበረሰብ አገልግሎት እና በምርምር ሥራ እምርታ ማሳየቱንም ገልጸዋል። አርሶ አደሮች ባበረከቱት መሬት ላይ የተመሠረተው የሰላሙ ዩኒቨርሲቲ አሁን የምርምር ዩኒቨርሲቲ መኾኑን አንስተዋል።

ከልሕቀት ማዕከላት እስከ አገልግሎት ሰጭነት ያካተቱ 22 ግቢዎች ያሉት አንጋፋ ተቋም መኾኑንም ገልጸዋል። ራስ ገዘ ለመኾን የሚያስችሉትን ሥራዎች እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከ13 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ወገኖች የጤና አገልግሎት እየሰጠ መኾኑንም አንስተዋለን። በየዓመቱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ታካሚዎችን እንደሚያስተናግድ ተናግረዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ እና የማስተማሪያ ሆስፒታሉ 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ስኬታማ እንደነበርም አንስተዋል። በምስረታ በዓሉ ሂደት ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውንም ገልጸዋል። መልካም ተሞክሮዎችን ያጋሩበት፣ መሪዎችን እና ባለውለታዎችን ያከበሩበት፣ የማኅበረሰቡን ችግር ለመቅረፍ ጥልቅ ውይይት ያደረግንበት፣ ችግር ፈቺ የተግባር አቅጣጫዎችን ያስቀመጥንበት ነበር ብለዋል።

ተቋም መፍጠር የቻሉ ሁነቶች መካሄዳቸውንም አንስተዋል። በዚህ ዓመት 22 ፕሮጄክቶችን ማስመረቃቸውን ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ ዛሬ ደግሞ በዩኒቨርሲቲው እና አጋር አካላት የሚሠሩ 26 ፕሮጄክቶች መሠረተ ድንጋይ ማስቀመጣቸውን ገልጸዋል። ፕሮጄክቶቹ በቀጣይ አምስት ዓመታት እንዲሚገነቡም ተናግረዋል።

ከሚገነቡ ፕሮጄክቶች መካከል ዘመናዊ የእናቶች እና የሕጻናት ሆስፒታል እንደሚገኝበት ገልጸዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ እና የማስተማር ሆስፒታሉ 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ተቋማዊ እና ሀገራዊ ፍሬዎች የታዩበት ክብረ በዓል እንደኾነም ተናግረዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እዚህ እንዲደርሰ ላደረጉ ሀገራት እና ተቋማትም ምስጋና አቅርበዋል። ድጋፋቸው ፍሬ ማፍራቱንም ተናግረዋል። አጋርነታቸውን እና ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ የማስተማሪያ ሆስፒታሉ 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በስኬት እንዲጠናቀቅ በገንዘብ ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበቅንጅት ከተሠራ ሕገ ወጥ የሰዎችን ዝውውር መቀነስ ይቻላል።
Next articleየጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዕድገት ምስጢሩ አጋር አካላትን ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ መፍጠር መቻሉ ነው፡፡