
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለዓመታት የተራቡትን አጉርሰዋል፣ የታረዙትን አልብሰዋል፣ የተጠሙትን አጠጥተዋል፣ መድረሻ የሌላቸውን አስጠልለዋል፣ ስለተራቡት ተርበዋል፣ ስለተጠሙት ተጠምተዋል፣ ስለታረዙት ታርዘዋል፣ ስለተቸገሩት ተቸግረዋል። ጧሪ የሌላቸውን ጡረዋል።
የአረጋውያን ጧሪያቸው፣ የሕጻናት አሳዳጊያቸው፣ የአዕምሮ ሕሙማን ጠባቂያቸው ናቸው። ወላጆቻቸውን ያጡ ሕጻናትን አሳድገዋል፣ ቀን ያጎደለባቸውን አረጋውያንን እንደ ልጅ ኾነው አኑረዋል። በጎዳና ላይ የወደቁ አዕምሮ ሕሙማንን አለሁ ብለው ሠብሥበዋል።
ሕይዎታቸውን ሙሉ ለአረጋውያን፣ ለሕጻናት እና ለአዕምሮ ሕሙማን ሰጥተዋል። ነፍሴ እነርሱን ባየች ጊዜ ሀሴትን ታደርጋለች፣ ስጋዬም ታርፋለች ይላሉ። እኛ እናስባለን፣ እግዚአብሔር ይፈጽምልናል፣ እኛ እንጀምራለን እግዚአብሔር ይጨርስልናል። ቋሚ ገቢ የለንም ግን በአምላክ ቸርነት ለአረጋውያን፣ ለሕጻናት እና ለአዕምሮ ሕሙማን የምናጎርሰው አጥተን አናውቅም ይላሉ። ይህ የነፍስም የስጋም ሥራ ነውና ሊገልጹት ከሚችሉት በላይ ደስታና ሃሴት አለው ይላሉ።
ብርሃን መልካሙ ይባላሉ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ጯሂት ከተማ የሚገኘው የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ምንዱባን የበጎ አድራጎት ማዕከል መሥራች እና ሥራ አሥኪያጅ ናቸው። የበጎ አድራጎት ማኅበሩ በ1999 ዓ.ም ነው የተመሠረተው። የበጎ አድራጎት ሥራውን ቤት ለቤት እየዞሩ አረጋውያንን እየረዱ እንደጀመሩት ያስታውሳሉ። አንድ ሁለት ተብሎ የተጀመረው የበጎ አድራጎት ሥራ አሁን ላይ 250 አረጋውያንን፣ ሕጻናትን እና የአዕምሮ ሕሙማንን በአንድ ማዕከል ይንከባከባል።
በቤተክርስቲያን አካባቢ ቁጭ ብለው ከአማኞች ምጽዋት የሚጠይቁ ወገኖች የበጎ አድራጎት ማዕከሉ እንዲመሠረት መነሻ ኾነውኛል ይላሉ። እነዚህን ወገኖች በበዓላት ቀን ጾም አስፈታ፣ ሲታመሙ አስታምም፣ ሲሞቱም እቀብር ነበር ነው የሚሉት። ይህም ሥራ በጎ አድራጎት ተግባር ማዕከል ለመመሥረት መነሻ ኾነ።
የበጎ አድራጎት ማኅበሩን ሲመሠርቱ በኪራይ ቤት ወገኖችን ይዘው ይኖሩ እንደነበር ነው የነገሩን። ቆይተው ግን መንግሥት ቦታ እንደሰጣቸው ነው የገለጹት። እኛ 250 ወገኖችን ለመመገብ፣ ለማልበስ እና ለማሳከም ቋሚ ገቢ የለንም፣ እግዚአብሔር ግን በቸርነቱ ይመግባቸዋል። አሳጥቶን አያውቅም ነው የሚሉት።
የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ለነፍሴ የሚሉ ወገኖች ይሰጡናል፣ በእርሷ ወገኖቻችንን እንደግፋለን ነው ያሉት። በበጋ ወቅት ወደ ገጠሩ እየወጡ ከአርሶ አደሮች እህል እንደሚሠበሥቡም ነግረውናል።
ማኅበሩን ከባለቤታቸው ጋር እንደመሠረቱት የነገሩን ብርሃን የአረጋውያንን፣ ሕጻናትን እና የአዕምሮ ሕሙማንን ድጋፍ ስናደርግ፣ ስንከባከብ ደስታ ይሰማናል፣ ሃሴት እናደርጋለን ነው የሚሉት። አሁን ላይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ በጎ ፈቃደኞች እንዳሉም ገልጸዋል።
ማዕከሉን የሚመግብልን አምላክ ነው። የዕለት ምግብ አያሳጣንም። ነገር ግን እንደ ሰው የያዙት ሲያልቅ እንደሚደነግጡ ጠቁመዋል። በነፍሳቸውም በስጋቻውም ሀሴትን ማድረግ የሚሹ ካሉ ማዕከሉን ይደግፉ ነው ያሉት።
የተፈጠረው የሰላም ችግር በጎ ፈቃደኞች እንደልብ እንዳይመጡ እንዳደረጋቸውም አንስተዋል። መልካም ማድረግ በሰማይም በምድር መልካም ዋጋ ያስገኛል፣ ኢትዮጵያውያን እንዲያግዙን እንጠይቃቸዋለን ነው ያሉት።
ሁሉም ለእናት፣ ለአባቱ፣ ለጎረቤት ይታዘዝ፣ ማኅበረሰቡን ያግዝ፣ በጎነት ታላቅ ጸጋ ነው፣ መልካምነት የሚኖሩት እንጂ በቃላት የሚገለጽ አይደለም ይላሉ። ወገኖችን እንደግፋቸው፣ አሳዳጊ የሌላቸውን ሕጻናት እናሳድጋቸው ነው የሚሉት።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ የማኅበራዊ ጥበቃ ጥናት እና ምርምር ቡድን መሪ ወይንሸት አያሌው የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ምንዱባን የበጎ አድራጎት ማዕከል ጧሪ እና ቀባሪ የሌላቸውን አረጋውያንን፣ አሳዳጊ የሌላቸውን ሕጻናትን፣ የአዕምሮ ሕሙማንን እያነሳ በተሻለ አኗኗር እንዲኖሩ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
አብዛኛውን ድጋፍ የሚያደርግላቸው የአካባቢው ማኅበረሰብ ነው፣ የወረዳው አሥተዳደር እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲም አልፎ አልፎ ድጋፍ ያደርጋሉ ነው ያሉት። የበጎ ፈቃደኞች መልካም ተግባር መኖሩ ነው እንጂ በተቋማቸው የሚደረግላቸው ድጋፍ የተጠናከረ አለመኾኑንም ገልጸዋል። በዞኑ ለችግር ተጋላጭ የኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። በተለይም በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለችግር ተጋላጭ የኾኑ ወገኖችን ለመደገፍ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን መደገፍ እንዳለባቸውም ገልጸዋል። ተቋማት፣ ባለሃብቶች፣ በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች የበጎ አድራጎት ማኅበራትን እና በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ የአረጋውያን እና የአካል አጉዳተኞች ጉዳይ ዳይሬክተር መንበሩ የወርቅ አጋር አካላትን በማስተባበር ለበጎ አድራጎት ማኅበራት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት። ለአረጋውያን እና ለአካል ጉዳተኞች በዓላት ሲከበሩ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
“አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች በመጀመሪያ ድጋፍ እንዲያገኙ የምንፈልገው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ኾነው ነው” ብለዋል። ቤተሰብን መሠረት ያደረገ ድጋፍ እንዲኖር ይፈለጋል፣ ከዚህ ሲያልፍ ደግሞ ከቀያቸው ሳይርቁ በማኅበረሰቡ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ነው የሚፈለገው ይላሉ። በማዕከል ኾነው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ማድረግ የመጨረሻው አማራጭ መኾኑንም ገልጸዋል።
ድጋፍ፣ ክትትል እና ቁጥጥር የማድረግ ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል። አካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን እንደሚሠሩም ገልጸዋል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥርዓት እንዲኾን እና ለወገኖች መድረስ እንዲቻል እንደሚሠራም ተናግረዋል።
አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች በርካታ ፍላጎት አላቸው ያሉት ዳይሬክተሩ ይህን ፍላጎታቸውን ላማሟላት ደግሞ ባለሙያዎች በሙያቸው፣ ጉልበት ያላቸው በጉልበታቸው፣ ዕውቀት ያላቸው በዕውቀታቸው፣ ገንዘብ ያላቸውም በገንዘባቸው ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት። ጥቂት በጎ አድራጊ ሰዎች ብቻ ለችግር ተጋላጭ ወገኖችን ሁሉንም ተደራሽ ማድረግ እንደማይችሉ ነው የተናገሩት።
የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ምንዱባን የበጎ አድራጎት ማዕከልን ማገዝ ለምትፈልጉ:- 0929070113
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን