
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የእድሜ እኩሌታቸውን ሀገራቸውን በቅንነት ሲያገለግሉ ኑረዋል። ቅን፣ ገራገር፣ ሰው ወዳድ እና ሰዎችም የሚወዷቸው ተግባቢ ናቸው። ብዙ ጊዜ ሕዝባቸውን በዕውቀታቸው እና በሚችሉት ሁሉ ለማገልገል ካላቸው ፍላጎት በመነጨ በአውራ ጎዳና ሥራ ላይ ተሠማርተው ሕዝብን የሚጠቅም ሥራ ሠርተዋል በደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ የነበሩት አቶ ፈንታ መስተሳኅል።
የሥራ ሁኔታቸው ከአንደኛው የሀገሪቱ ጫፍ ወደሌላኛው ጫፍ የመንቀሳቀስ ዕድል ይሰጣቸው ነበርና ያላዩት እና ያልገቡበት የኢትዮጵያ ቀየ አልነበረም። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት እንደኾነ ጠንቅቀው ያውቃሉ።
የሀገር ፍቅርንም የሥራ ሁኔታቸው እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል። አቶ ፈንታ መሥተሳኅል ሁሌም የሀገራቸው ድህነት እና የሕዝቡ አለመበልጸግ ያሳዝናቸው ነበር።
በተለይም እንደ ዓባይ አይነት ትልቅ ሃብት የያዘች ሀገር እንዴት ሕዝቧን መመገብ እንደተሳናት እያሰቡ ሲቆጩ ኑረዋል። የዓባይ ውኃ ለግብጻውያን እና ሱዳናውያን እንጀራ ሲኾን ለምን ለሀገሩ ጥቅም አልዋለም የሚለው እንቆቅልሽ እንዴት እንደሚፈታ ሲያወጡ ሲያዎርዱ ነው የኖሩት።
አቶ ፈንታ ለሀገራቸው የቻሉትን ሁሉ አድርገው ጡረታ ለመውጣት ተገደዱ። ምንም እንኳን ጡረታ ቢወጡም ሀገራቸውን በምን መንገድ ማገዝ እንዳለባቸው ሁሌም ማሰባቸው አልቀረም።
በዚህ ሂደት ሳሉ ታዲያ ጡረተኛው አቶ ፈንታ አንድ ቀን ምሳ ለመብላት በቤታቸው ማዕድ በተቀመጡበት ጊዜ በቴሌቪዥን አንድ ጥሩ ነገር ተመለከቱ። እድሜ ዘመናቸውን የሚመኙትን መረጃ ነበር።
ዘመኑ 2003 ዓ.ም ነው ይላሉ ሁኔታውን ያስታወሱን ሦሥተኛ ልጃቸው ቤተልሄም ፈንታ። ቤተልሄም እንደነገሩን ዜናውን ምሳ እየበሉ ሲሰሙ አባታቸው ማመን እንዳቃታቸው እና እንደ ሕጻን ልጅ ከመቀመጫቸው ተነስተው ደስታቸው በመግለጽ ሁሌም ሲመኙት የነበረ ጉዳይ መኾኑን ነገሩን ይላሉ።
ከመረጃው ባሻገር እንዴት ማገዝ እችላለው የሚለው ላይ መወያየት እንደሚፈልጉ ገለጹ። የጡረታ ደመወዛቸውን ለመስጠት ማሰባቸውን ሲገልጹ ሙሉ ቤተሰቡ በደስታ መቀበሉን ያስታውሳሉ።
የአባታቸው ጡረታ 1 ሺህ 600 ብር እንደነበረ የነገሩን ወይዘሮ ቤተልሄም ከዚህም የ1 ሺህ ብር ቦንድ በየወሩ ለመግዛት በቤተሰብ ተወስኖ የቦንድ ግዥው መፈጸም ጀመረ ነው የሚሉት። እኒህ ሰው ምኞታቸው ዓባይ ተጠናቅቆ ሲመረቅ ማየት ነበር። ነገር ግን ይህ አልኾነም። ዓባይ ሊጠናቀቅ ትንሽ ሲቀረው ሞት ቀደማቸው። በሞት አፋፍ ላይ ኾነው ግን ዓባይን አልዘነጉትም። ለልጆቻቸው የኑዛዜ ቃል አስቀመጡ።
ኑዛዜው!
ልጃቸው አባታቸው የሰጧቸውን የኑዛዜ ቃል ኪዳን ስታስታውሱ አባቴ ይህችን ዓለም እየተሰናበተ እጀን ይዞ ልጀ የዓባይን ነገር አደራ፤ እንዳይቋረጥ ለፍጻሜ አብቁት እኔ ለእናንተ አደራ ሰጠሁ ብሎ ነፍሱ ከስጋው ተለየች ነው ያሉት።
ዓባይ እንዲህ ከዳር ሲደርስ አባቴ አይቶት ቢሞት ብለው እንደሚቆጩም ነግረውናል።
የኑዛዜው አደራ ምን ላይ ነው?
የጀግና ልጅ ጀግና ነው የግድቡ ፍጻሜ በልጆቹ የአደራ ቅብብሎሽ ዳር እንደሚደርስ አትጠራጠር ያሉት ወይዘሮ ቤተልሄም የአባታቸው የቦንድ ግዥ እንዲቀጥል ከባንክ ጋር እየተነጋገሩ እንደኾነ ነግረውናል።
ከቤተሰብ እንደሳቸው የሀገር ፍቅር የገባው ይኖር ይኾን?
የፈንታ መስተሳኅል ልጆች ሀገራቸውን እንዲወዱ ተደርገው ያደጉ በመኾናቸው ሁሉም ከራሱ ሀገሩን የሚያስቀድም እንደኾነ ገልጸዋል። በቀጣይም በሌሎች ልማቶች ከሀገራቸው ጎን ተሰልፈው እንደሚሠሩ ነግረውናል።
የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የአማራ ክልል ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓባይነህ ጌጡ የዓባይ ግድብ ከተጀመረ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያውያን የራሳቸው ግድብ እንደኾነ ተገንዝበው ግድቡን ለመገንባት ሰፊ ርብርብ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን ከሕጻን እስከ አዋቂ ለልማት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳዩበት ግድብ ነው ያሉት ኀላፊው አንድነት ብዙ ለውጥ እንደሚያመጣ የታየበት ሥራ እና ተሳትፎ ነበር ብለዋል።
ቀጣይ እንደ ዓባይ አይነት ግድብ ቢጀመር ኢትዮጵያውያን በኅብረት እንደሚጨርሱት የተረጋገጠበት እንደኾነም ጠቁመዋል።
በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የሕዝብ ተሳትፎ ከጫፍ ጫፍ የነበረ ቢኾንም የአንዳንድ ሰዎች ሥራ ግን ጎልቶ እንደታየ ነው ያብራሩት።
ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ እስከአሁን ድረስ አስተዋጽኦ እያደረጉ ያሉ ግለሰቦች እና ተቋማት መኖራቸውን የተናገሩት ኀላፊው ለእነዚህም ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ የምስክር ወረቀት እና ዕውቅና መሥጠቱን ነው የነገሩን።
አቶ ፈንታ መስተሳኅል ዕውቅና ከተሰጣቸው ግለሰቦች መካከል እንደኾኑም ተናግረዋል። ግለሰቡ በጡረታ እያሉ ያደረጉት ተሳትፎ እና የነበራቸው ተቆርቋሪነት ምሳሌ የሚኾን እንደኾነም ጠቁመዋል።
ዕውቅናውንም በተወካዮቻቸው አማካኝነት መስጠታቸው ነው የነገሩን። ግለሰቡ እስከ ሕይወት ፍጻሜያቸው ድረስ 168 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውንም ነው ያብራሩት።
ዘጋቢ፦ ምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን