ዓባይ በቤቱ አድሯል!

71

ባሕር ዳር: ሐምሌ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጥንቶቹ ዜማዎች ትዝታ ኾነዋል፤ የጥንቶቹ ግጥሞች ለታሪክ ተጽፈዋል፤ ለነበር ተከትበዋል፤ የትናንቱን ለማስታወስ ተቀምጠዋል። አሁን ዓባይ አይንከራተትም፣ አሁን ዓባይ ማደሪያ አያጣም። አሁን ዓባይ ግንድ ይዞ አይዞርም። አሁን ዓባይ የሀገሩን ለም አፈር ተሸክሞ አይጓዝም። እናቱንም አይበዘብዝም።

አሁን በፈለቀባት ምድር፣ በጎለመሰባት፣ በሚከባት፣ ምስጢር ይዞ በወጣባት፣ ትንቢት ይዞ በኖረባት፣ ቃል ኪዳን በተቀበለባት ሀገር ያድራል። ዛሬ ትናንት አይደለም፣ ዛሬ እንደ ትናንት አይኖርም። ዛሬ ዘመን ተቀይሯል። ግዮን በእትብቱ ምድር አድሯል። ከፈለቀባት ምድር ልጆች ጋር በቃል ኪዳን ተሳስሯል።

ለዘመናት በዋሽንት እያዜሙ የሸኙት እረኞች፣ በማሲንቆ እያጀቡ የተሰናበቱት ዓለም አጫዋቾች፣ ክረምት በመጣ ቁጥር ማዶና ማዶ ኾነው እስኪጎድል የጠበቁት የሀገሬው ደጋግ ሰዎች፣ በዙሪያው በሬዎቻቸውን ጠምደው በፉጨት ያሞገሱት፣ በቀረርቶ ያወደሱት፣ በጅራፍ ድምጽ ያደመቁት ገበሬዎች የተመኙት ደርሷል።

ግዮንን የሚሸኙት ሳይኾን አብረው የሚባጁት፣ አብረው የሚኖሩት ኾኗልና። እንደ ጥንቱ በስስት የሚሰናበቱት፣ በናፍቆት የሚለያዩት ሳይኾን በፍቅር አብረውት ውለው የሚያድሩት፣ አብረውት የሚከርሙት ኾኗልና።

ገና ጥንት ሥልጣኔ እንደ ወራጅ ውኃ ያፈሰሱ፣ በኃያልነት ጎዳና የተመላለሱ ነገሥታት በግዮን ላይ ያሰቡት ተፈጽሟል። በግዮን ላይ ያለሙት ሕልም እውን ኾኗል። ዛሬ መቃብር ፈንቅለው ባይወጡም፤ ከአፈር ተለይተው ባይመጡም። አጽማቸው የሠሩትን ልጆቻቸውን ያመሰግናል። በመቃብር ኾነው ይመርቋቸዋል። እንኳንም ወለድኩ ብለው ይመኩባቸዋል። በሰማይ ያለች ነፍሳቸው ደስ ትሰኛለች፤ ሀሴትንም ታደርጋለች።

ከጥንት ጀምሮ ቅኔ የተቀኙለት፣ ምስጢር የቋጠሩበት፣ ትንቢት የተነበዩለት ሊቃውንት ያሉት ደርሷል። የተናገሩት ተፈጽሟል። ለሁሉም ጊዜ አለው እንዳለ ጠቢቡ ጊዜው ደርሶ ሁሉም ኾኗልና። ዓባይ ትናንት ትንቢት ነበር ዛሬ እውነት ኾኗል። ትናንት ሕልም ነበር ዛሬ ገቢር ኾኗል። ትናንት ተስፋ ነበር ዛሬ የሚጨበጥ ሐቅ ኾኗል። ትናንት ቢኾን ነበር ዛሬ ግን የኾነ የተደረገ ኾኗል።

አሁን ዓባይን የነካ ወዮለት የሚሉ የጠላት ፉከራዎች፣ ማስፈራሪያዎች እንደ ጉም በነው፣ እንደ ጭስ ተነው ጠፍተዋል፡፡ አሁን ዓባይ የተነካለት ምድር በእሳት ጅራፍ ትገረፋለች ያሉ ሁሉ አንገታቸውን ደፍተዋል። የትናንት ፉከራቸውን እያሰቡ አፍረዋል። አሁን ዓባይን የነካ ዘመኑ ትፈጸማለች ያሉ ሁሉ መደበቂያ ዋሻ አጥተዋል። መከለያ ጥላ ተቸግረዋል።

መከራ የሚያጸናቸው፣ ፈተና የሚያበረታቸው፣ እንኳን የፎከረ የወረወረ የማያስደነግጣቸው፣ አልፍ አዕላፍ ጠላት ቢነሳ የማያሰጋቸው፣ ጠላትን ድል ማድረግ ከጥንት ጀምሮ የተሰጣቸው፣ ጽናት፣ አንድነት፣ አብሮነት፣ ኅብረት፣ ጀግንነት፣ አትንኩኝ ባይነት እና ድል አድራጊነት የተቸራቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉንም ችለው አድርገውታል። በዓባይ ያሰቡትን አሳክተውታል። የጀመሩትን ፈጽመውታል።

ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ኢትዮጵያ ግብጽን እንደፈጠረቻት እና እንዳሠለጠነቻት በተሰኘው መጽሐፋቸው ግብጽ ራሷን ብቻ በመውደድ እና ከመስገብገቧ የተነሳ ኢትዮጵያ በገዛ ውኃዋ በዓባይ እንዳትጠቀም አያሌ አሻጥሮችን እና ስልቶችን ከውና ነበር ይላሉ።

ከእነዚህ ስልቶች እንዱ ኢትዮጵያን ሳትጨምር እርሷ ቀንድ ኾና ሱዳንን ጭራ አድርጋ በእንግሊዝ ፈቃጅነት አብዛኛውን ውኃ ለራስዋ፣ በጣም ትንሹን ደግሞ ለሱዳን በመተው ከእንግሊዝ ጋር ያዋዋለችው የስግብግብነት ውል ነው። ውሉንም አንድ ጊዜ ብቻ አይደለም ሁለት ጊዜ ተዋዋለች እንጂ።

ይህ ፍርደ ገምድል ውል ለዓባይ ውኃ ከ85 በመቶ በላይ የምታበረክተውን ኢትዮጵያን ያላካተተ ነበር። ይህ ብቻ አይደለም የግብጽ መሪዎች ዓባይን ለጥቅም የሚያውል ከተገኘ እና ዓባይ ከጎደለብን ጦርነት እንከፍታለን እያሉ ሲዝቱ ኖረዋል ነው የሚሉት።

በጠላቶቿ ማስፈራሪያ የማትሸበረው እና በጠላቶቿ ጦር የማትበገረው ኢትዮጵያ ግን ጥቅሟን የሚጻረር የትኛውንም አካሄድ አልቀበልም አለች። ግብጽ ኢትዮጵያ ተረጋግታ የዓባይ ግድብን እንዳትገድብ ነጻ አውጭ ድርጅቶች ነን የሚሉ ታጣቂዎችን ስታስታጥቅና ግጭት ስትቀሰቅስ ኖራለች ይላሉ።

ግብጽ ታጣቂዎችን እያስታጠቀች በኢትዮጵያ ግጭት የምትቀሰቅሰው ውኃው ይቀንስብኛል ብላ ሳይኾን ኢትዮጵያ ግድቡን ገድባ ከበለጸገች በአካባቢው የእኔ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ዋጋ ያጣል ብላ በመፍራት ነው።

ኢትዮጵያ ግድቧን እንዳትገድብ እና እንዳትሻሻል ማንም በየፊናው አሻጥር ቢሠራ በመጨረሻም እሷ የዘመናት ምኞቷን እና እቅዷን ተግብራዋለች ብለዋል ፕሮፌሰር ፍቅሬ።

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር ቡሩክ ኃይሉ ኢትዮጵያ ፈጣሪ እና ተፈጥሮ የሰጣትን ጸጋ እንዳትጠቀም ብዙ ተሠርቶባታል ይላሉ፡፡ በተለይም ከሱዳን እና ከግብጽ ፈተና ይገጥማት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የዓባይ ምንጭ ናትና የዓባይን ምንጭ ለመያዝ ተዳጋጋሚ ጦርነቶች ተካሂደዋል፡፡ ነገር ግን አንዳቸውም አልተሳኩም፡፡ ሁሉም በኢትዮጵያውያን ጀግንነት ተመክተዋል ነው የሚሉት።

አሁንም በዚህ ዘመን ግብጻውያን ኢትዮጵያ የዓባይ ግድብን እንዳትሠራ ያላደረጉት ነገር የለም፤ ነገር ግን ያደረጉት ሁሉ አልተሳካም፡፡ ዓባይ በፈተናዎች አልፎ የተገነባ ነው ብለዋል። የሕዳሴ ግድብ ብዙ የፈተና ትብታቦችን የበጣጠሰ ነው፡፡ ብርቱ ሕዝብ እና ብርቱ መሪ ባይኖር ኖሩ የሕዳሴ ግድብ እንዲሁ ይቀር ነበር ነው የሚሉት፡፡

የአፍሪካ ማማ የኾነችው ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድቡ አያሌ ጥቅሞችን ታገኛለች፡፡ ከሕዳሴው ግድብ ለመጠቀም የሄደችባቸው ጉዞዎች ግን አድካሚ እና ፈተናዎች የበዙባቸው ነበሩ ብለዋል።

ግድቡ ኢትዮጵያ መብቷን ለማስከበር ማንም እንደማያቆማት ያስመሰከረችበት ሕያው ምስክር ነው፡፡ ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ ኾና ሥራዋን ሠርታ ለዚህ ያበቃችው ታላቅ ሥራ ነው፤ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የሠሩት ነው።

ተባብረን እንደተነሳን፣ ተባብረን ለውጤት እንደምንበቃ ያሳየንበት ነው፤ የሕዳሴ ግድብ ማንም እንደማያስቆመን ማሳያ ነው ይላሉ፡፡

የሕዳሴ ግድብ አሁንም ተባብረን በአንድነት ከሠራን ትልቅ ደረጃ ላይ እንደምንደርስ ማሳያ ነው የሚሉት ምሁሩ ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ማድረግ የምትፈልገውን በዲፕሎማሲ ግንኙነቷ ማሳወቋን፣ ግልጽ አቋሟን ማሳየቷን፣ በግልጽ መራመዷን ነው ያነሱት፡፡

የሕዳሴ ግድብ የምንኮራበት፣ የልጅ ልጆች የሚኮሩበት፣ በጦርነት ነጻነታችን እንዳስከበርን ሁሉ በምጣኔ ሃብት ነጻነታችንን ያስከበርንበት፣ እንደማንበገር ያሳየንበት ነው ይላሉ፡፡

የሕዳሴ ግድቡ ሌሎች ሀገራትም መብታቸውን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ብርታት እና መነሳሳት የሚፈጥር መኾኑንም አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያን የሚያስፈራሩ ሀገራት ምንም እንደማያመጡ አመለካከቱን ኢትዮጵያ ሰብራዋለች፣ እንኳን ለራሷ ለሌሎችም አለኝታ ኾናለች ይላሉ።

ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ልምድ ያላት ሀገር ናት ያሉት ምሁሩ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ታሪክ ከፍ ያደረገ፣ ወገኖችን የሚጨምር፣ የኢትዮጵያን ብልሃት የተሞላበት የዲፕሎማሲ ሥራ ያሳየ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን የካበተ እና ከትውልድ ትውልድ ሲቀባበል የመጣ የዲፕሎማሲ እውቀት አላቸው። ከኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ልምድ እና ስኬት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ልምድ መውሰድ አለባቸው ነው ያሉት፡፡ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጥበብ አያሌ ጫናዎችን መቀነሱንም ተናግረዋል፡፡ ችግሮችን እየፈታ ውጤት አምጥቷል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ድንቅ ዲፕሎማቶችን ያፈራችበት ዘመንም መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ፊት በውጭ ግንኙነቷ የሚደንቅ ሥራ የሚሠሩ ልጆች አፍርታለች ነው ያሉት፡፡ የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ሲናፍቁት የኖሩትን የኃይል አቅርቦት ችግር የሚፈታ፣ ድህነትን የሚያስቀር ነው ይላሉ፡፡

ሰላም የሌለው ሀገር ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት አይኖረውም ያሉት ምሁሩ ኢትዮጵያ ዕድገቷን ለማረጋገጥ ሰላም ያስፈልጋታል ነው የሚሉት። ሰላም ላይ በመመስረት ትውልድ የሚያሻግሩ እና የሚያስተሳስሩ የልማት ሥራዎችን መሥራት አለብን ብለዋል፡፡

ኅብረት፣ አብሮ መሥራት ግድ ይላል፤ ሀገርን ከማንኛውም የፖለቲካ አስተሳብ ከፍ አድርጎ ማየት ይገባል፤ በሀገራዊ ጉዳይ የእገሌ ነው አይባልም ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያን እናት ሀገርን ማስቀደም ይገባል፤ ይህ ካልኾነ እናትን እንደመበደል፣ እንደመጉዳት ይቆጠራል፤ የፈለገው ልዩነት ይኑር ኢትዮጵያ ከማናችንም በላይ ናት፤ ምንም አይነት ችግር ይኑር ችግርን ፈትቶ ኢትዮጵያን በጋራ ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት፡፡ እናት ኢትዮጵያ ላይ ምንም አይነት ስስት ሊኖር አይገባም ይላሉ።

የተባበሩ ችግርን ይሻገራሉ። በአንድነት የጸኑ ሕልማቸውን ዕውን ያደርጋሉ። ኅብረታቸውን ያጠነከሩ ከፍ ብለው ይኖራሉ። ሀገራቸውንም ከፍ ከፍ ያደርጋሉ።

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበፍኖተ ሰላም ከተማ የተለያዩ የመሠረተ ልማቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ።
Next articleልጆቼ ዓባይን አደራ