
ፍኖተ ሰላም፡ ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር በ2017 በጀት ዓመት በኅብረተሰቡ ተሳትፎ፣ በአጋር ድርጅቶች እና በመንግሥት ወጭ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ተመርቀዋል።
የሰላም ሁኔታውን ከማረጋጋት ሥራ ጎን ለጎን ከ76 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የጠጠር መንገድ፣ የቢሮ እድሳት፣ የጤና ጣቢያ እና የትምህርት ቤት ግንባታ እንዲሁም ሌሎች ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን የፍኖተሰላም ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ጊዜው ደግአረገ ተናግረዋል።
ኅብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ፕሮጀክቶችን ከመጀመር ባሻገር በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ የፍኖተ ሰላም ከተማ ነዋሪ ኡመር ሁሴን እና ፈንታ እንዳዬ የተሠሩ የልማት ሥራዎች የኅብረተሰቡን ችግሮች የፈቱ መኾናቸውን ተናገረዋል። ሌሎች የተጀመሩ ፕሮጀክቶችም እንዲጠናቀቁ ጠይቀዋል።
ለዚህ ደግሞ ኅብረተሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በዞኑ የሰላም ሁኔታውን ከማረጋጋት ጎን ለጎን የኅብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እየተሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ አጉማሴ አንተነህ ተናግረዋል።
መሪዎች ያለፉት ጊዜያትን በሚያካክስ መንገድ ሰላሙን እያረጋገጡ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መኾኑን አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን