የሳንባ ካንሰር እንደ ሀገር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

18

አዲስ አበባ: ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ እና ከማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ጋር በመተባበር የዓለም የሳንባ ካንሰር ቀንን እያከበረ ነው። እንደ ሀገር የሳንባ ካንሰር ስርጭትን ለመግታት ከቅድመ መከላከል እስከ ድኅረ ሕክምና ክትትል ድረስ በርካታ ተግባራት መሠራቱን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል::

የሳንባ ካንሰር በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት ከሚታወቁ የካንሰር አይነቶች አንዱ ሲኾን በካንሰር ምክንያት ከሚከሰተው የሞት ምጣኔ ደግሞ በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ፕሬዝዳንት ራሔል አርጋው (ዶ.ር) ማኅበራቸው የሳንባ ካንሰርን አስቀድሞ ለመከላከል በጤናው ዘርፍ ውስጥ በማማከር ምርምሮችን በማድረግ እና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን በማስፋት ከአጋር አካላት ጋር በጋራ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል::

የሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም የሳንባ ካንሰር እና ሌሎች የሳንባ በሽታዎችን አስቀድሞ መለየት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ጥናቶች እየተደረጉ እንዳሉም ፕሬዝዳንቷ ገልጸዋል።

የማቲዎስ ወንዱ ካንሰር ሶሳይቲ መሥራች እና ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ወንዱ በቀለ “የሳንባ ካንሰር እንደ ሀገር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል” ብለዋል።

ይህንንም ቅድመ ምርመራ በማድረግ እና የቅድመ ጤና ክትትልን በማጠናከር እና ራስን ከሱስ በማራቅ ጤናን መጠበቅ ይገባል ነው ያሉት። ይህ ሲኾን ጤናማ እና ሀገር ተረካቢ ትውልድን መፍጠር ይቻላል ብለዋል።

በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች ዴስክ ኀላፊ ዶክተር ሰላማዊት አየለ ሚኒስቴሩ የሳንባ ካንሰር ቅድመ መከላከል እና ድኅረ ሕክምናን አስመልክቶ ግንዛቤ ለመፍጠር ከአጋር አካላት ጋር እየተሠራ እንደኾነ ተናግረዋል።

ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች እንደ ሀገር እየጨመሩ የመጡ መኾኑን የገለጹት ኀላፊዋ የሳንባ ካንሰር ሕክምና ካንሰሩ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ ካለው የስርጭት ደረጃ ጋር የተቃረነ በመኾኑ ኅብረተሰቡ ቅድመ ምርመራ ማድረግ አለበት ነው ያሉት። የጤና ሚኒስቴር የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የሳንባ ካንሰር ቀን በዓለም ለ14ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ2ኛ ጊዜ “የሳንባ ካንሰርን ሳይባባስ እና ሳይሰራጭ በምርመራ መለየት ይቻላል” በሚል መሪ መልዕክት በፓናል ውይይት እየታሰበ ነው።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበአማራ ክልል በ32 መናኸሪያዎች የኢ-ትኬቲንግ አገልግሎት እየተሰጠ ነው።
Next articleበፍኖተ ሰላም ከተማ የተለያዩ የመሠረተ ልማቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ።