በአማራ ክልል በ32 መናኸሪያዎች የኢ-ትኬቲንግ አገልግሎት እየተሰጠ ነው።

6

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ባለሥልጣን በባሕርዳር ከተማ ያሥገነባቸውን የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ጎብኝቷል።

የአማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ባለሥልጣን ኀላፊ ዘውዱ ማለደ በአማራ ክልል ያሉት የሕዝብ ትራንስፖርት ሰጭ መናኸሪያዎች ከዚህ በፊት ኅብረተሰቡን ለእንግልት እና ለንብረት መጥፋት ያጋልጡ እንደነበር ተናግረዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ እና የተሳለጠ አገልግሎት ለመሥጠት በቴክኖሎጅ የታገዘ የኢ-ትኬቲንግ ሲስተምን ለመተግበር ሲሠራ መቆየቱን አመላክተዋል።

በ2016 ዓ.ም በስድስት መናኸሪያዎች አገልግሎቱ መጀመሩን አንስተዋል። በአሁኑ ወቅት በክልሉ በ32 መናኸሪያዎች በኢ-ትኬቲንግ አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። በደረሰኝ ትኬት እንዲቆርጥ፣ በወንበር ልክ እንዲሳፈር እና ከሚደርስበት ቦታ በአግባቡ እንዲደርስ የሚያስችል አሠራር መኾኑን ነው የገለጹት።

ባለሥልጣኑ ተግባራዊ ያደረገው የኢ-ትኬቲንግ ሥራ ለኅብረተሰቡ ዘመናዊ አገልግሎትን ከመሥጠት ባለፈም የሥራ ዕድል እየፈጠረ መኾኑን ጠቁመዋል።

ለአብነትም 12 ድርጅቶችን በማሣተፍ ለ325 የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ኢንጅነሪንግ ባለሙያዎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለም አስረድተዋል።

ባለሥልጣኑ በቀጣይም በክልሉ ባሉት 252 መናኸሪያዎች በማዳረስ አገልግሎት ለመሥጠት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

የዋልያ ቴክኖሎጅ ምርቶች እና የመንገደኞች ፕሮጀክት ዳይሬክተር ፋሲል መኩሪያ ኢ-ትኬቲንግ ሲስተም የተሠራው መንገደኞች ከየትኛውም ቦታ ኾነው ወደ ሚፈልጉበት ቦታ ለመጓዝ ትኬት የሚቆረጥበት ሥርዓት እንደኾነ አብራርተዋል።

ሲስተሙ መንገደኞች የሚሄዱበት ቦታ፣ የሚጓጓዙበትን የመኪና አይነት፣ የሚከፍሉትን የገንዘብ መጠን፣ የወንበር ቁጥር እና ሌሎችንም መረጃዎች የያዘ መኾኑንም አስረድተዋል።

በባሕርዳር መናኸሪያ ሲሥተሙን በመጠቀም አገልግሎት ሲሰጡ አሚኮ ያገኛቸው የመናኸሪያው ሠራተኛ ሮዛ ደስታ ሲስተሙ ወደ ሥራ በመግባቱ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል።

በሲስተሙ ትኬት ቆርጠው ለመጓዝ ሲሳፈሩ አሚኮ ያገኛቸው ሶስና ደሳለኝ ደግሞ በፊት ግፊት እንደነበር ገልጸዋል።

እቃ ይጠፋ እና በመንገድ ላይም አላሥፈላጊ ጫና ይደርስባቸው እንደነበር ጠቁመዋል። ከመናኸሪያ ውስጥም ከፍተኛ እንግልት እና ወከባ ሲደርስ እንደነበር አንስተዋል።

“ሲስተሙ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ ግን እራሳችን ትኬት ቆርጠን፣ የመኪናውን አይነት አይተን ነው የምንሳፈር” ነው ያሉት።

የሚረብሽም ኾነ የሚጋፋ የለም፤ በዚህም ለተሳፋሪዎች እፎይታን የሰጠ አገልግሎት እያገኙ እንደኾነም ገልጸዋል።

ሌላኛው ተሳፋሪ መላዕከ ሰላም አፈወርቅ ወንድማገኝ ከዚህ በፊት በመናኸሪያ ውስጥ ለመሳፈር አስቸጋሪ እንደነበር አንስተዋል።

ከታሪፍ ውጭ ክፍያ እንዲከፍሉ ሲገደዱ መቆየታቸውንም ጠቁመዋል። ከታሪፍ ውጭ አልከፍልም የሚል ካለ መንገድ ላይ ውረድ ተብሎ ይንገላታ ነበር ብለዋል።

በትርፍ እየተጫነ ለነፍሰጡሮች ሳይቀር ችግር ኾኖ ነበር ይላሉ። አሁን ላይ ግን ይህንን ሁሉ ችግር እንዳቃለለ እና ጥሩ አገልግሎት እየተሰጠ መኾኑን ነው የተናገሩት።

ባለሥልጣኑ የመንጃ ፈቃድ ፈተና የሚሰጥባቸውን ማዕከላት በቀጥታ የሚቆጣጠር፣ ሕጋዊ የመንጃ ፈቃድን ማረጋገጥ የሚያስችሉ እና ሌሎችንም ሲስተሞች በማስለማት እየተገበረ መኾኑም ተመላክቷል።

ዘጋቢ:-አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር ማሻገርን በቅንጅት መከላከል ይገባል።
Next articleየሳንባ ካንሰር እንደ ሀገር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።