
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ውስጥ የሚካሄደውን በሰው የመነገድ፣ በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር የማሻገር፣ ተዛማጅ ወንጀሎችን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት የተቋቋመው ክልላዊ የትብብር ጥምረት የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ተካሄዷል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም እንዳሉት በሰው መነገድ እና በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር ማሻገር ዘመናዊ ባርነት በመኾኑ ችግሩን በቅንጅት መከላከል ይገባል።
ሰዎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የመኖር መብታቸው ተፈጥሯዊ ቢኾንም ሁሉም ነገር የሚሳካው ሕግ አክብረው ሲገኙ ነው ብለዋል። በሕገ ወጥ መንገድ መንቀሳቀስ ግን ዘርፈ ብዙ ጉዳት ያስከትላል ነው ያሉት።
በአሁኑ ሰዓት በሰው የመነገድ፣ ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና ተያያዥ ወንጀሎች በዓለም ላይ እየጨመሩ መምጣታቸውንም ጠቁመዋል። ወንጀሎቹ የሚያስከትሏቸውን ከፍተኛ የኢኮኖሚ፣ የማኀበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች በመረዳት ሀገራዊ ሕጎች ወጥተው ተግባራዊ እየተደረጉ መኾኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ወንጀሎቹን ከዓለም ማኀበረሰብ ጋር ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ዓለም አቀፍ ሕጎችን ተቀብላ በማጽደቅ እየተገበረችው ትገኛለች ነው ያሉት።
የአጋር ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ማኀበር ፕሬዝዳንት አበራ አደባ (ዶ.ር) በአማራ ክልል የአሠራር ኅብረት፣ ቀናነት እና አንድነት በመኖሩ በሰው የመነገድ፣ በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር የማሻገር እና ተዛማጅ ወንጀሎችን የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራውን አያከብደውም ነው ያሉት። የአጋር ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ማኀበርም ችግሩን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ይሠራል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!