
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ ሙጭት ተገኘ ይባላሉ፤ ከረጅም ዓመታት ጀምሮ በባሕር ዳር ከተማ የቀን ሥራ እየሠሩ በመተዳደር እንደሚኖሩ ነግረውናል፡፡
ወይዘሮዋ ይኖሩበት የነበረው ቤት ጣራው በጣም ዝቅተኛ እና ፍሳሽ ይበዛበት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
ክረምት ሲመጣ የነበረባቸውን መሳቀቅ በትካዜ ሲገልጹ በቀን ወደ ሥራ ሲወጡ ቤታቸው ጎርፍ ሞልቶበት መሶባቸው ሳይቀር ፍሳሽ ይገባው እንደነበር፤ ሌሊት መኝታ አጥተው ጥግ ይዘው ይቀመጡ እንደነበር እና የገባውን ጎርፍ ሲያፋስሱ ያድሩ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ዛሬ ግን የባሕር ዳር ከተማ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ከባሕር ዳር ከተማ አረጋውያን ማኅበር ጋር በመተባበር ቤታቸውን አፍርሶ በመሥራት በስሚንቶ ወለሉን ሊሾ እንዳደረገላቸው ጠቁመዋል።
የሚተኙበት አልጋ እስከ ፍራሹ እንዲሟላ በመደረጉም ደስተኛ መኾናቸውን ለአሚኮ ገልጸው ለተሠራው በጎ ተግባር አመሥግነዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አረጋውያን ማኅበር ሠብሣቢ መቶ አለቃ ብርሃኑ ሲሳይ ማኅበሩ ከዚህ በፊት ለደካሞች እና አረጋውያን የበዓል መዋያ ገንዘብ ይደግፍ ነበር፡፡
አሁን ግን ከዚህ በፊት የክልሉ አረጋውያን ማኅበር ለአቅመ ደካሞች ቤት ሠርቶ ሲያስረክብ እኛስ የአቅማችን ለምን ይህን አናደርግም በሚል መንፈሳዊ ቅናት በመነሳሳት ከሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ጋር በመተባበር መሥራታቸውን ነው የጠቆሙት፡፡
“ዛሬ ያገኘነውን ደስታ በምንም መለካት አይቻልም፤ በቀጣይም ቀድሞ ዕቅድ በመያዝ የተቸገሩ ወገኖቻችንን ለማገዝ አጠናክረን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ በ2017 ዓ.ም በክረምት በጎ አድራጎት ተግባር ሰፊ ሥራዎች መሥራታቸውን ተናግረዋል፡፡
የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ ግለሰቦችን ቤት በማደስ እና አዲስ ቤቶችን ሠርቶ በማስረከብ በንቅናቄ የተጀመረ ነው፡፡
የክረምት በጎ ፈቃድ በጎነት ጎልቶ የሚታይበት ተግባር በመኾኑ በቀጣይም በርካታ በጎ ፈቃድ ሰጭ የማኅበረሰብ ክፍሎችን፣ ወጣቶችን እና የተለያዩ ማኅበራትን በማሳተፍ የደካማ ቤቶች ጥገና፣ የአልባሳት ድጋፍ፣ የትምህርት መማሪያ ቁሳቁስ እና ሌሎች ድጋፎችን በሰፊው እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡
የክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራ እንደ ከተማ አሥተዳደሩ 380 ቤቶችን የማደስ እና 120 ቤቶችን በአዲስ ለመሥራት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ማኅበረሰቡን በማስተባበር የሁሉንም ችግር መቅረፍ ባይቻል እንኳ ችግሮችን በመቀነስ እና አብሮነትን በማሳየት በጎነት ጎልቶ የሚወጣበት መኾን እንዳለበት አብራርተዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሰናይት በዬነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን