በኅብረተሰቡ ውስጥ የተከሰቱ የጤና ችግሮች ላይ ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል፡፡

12

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ያለፈው በጀት ዓመት ሪፖርትም በመድረኩ ቀርቧል፡፡

ባለፈው በጀት ዓመት በክልሉ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ ምዕራብ ጎጃም እና የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞኖች እንዲኹም ከከተሞች የባሕር ዳር ከተማ ከፍተኛ የወባ ስርጭት ያለባቸው መኾኑ ተገልጿል።

አጠቃላይ በክልሉ በወባ በሽታ ከተያዙት 11 ነጥብ 9 በመቶ ከአምስት ዓመት በታች የኾኑ ሕጻናት እና 1 ነጥብ 2 በመቶ የሚኾኑት ደግሞ ነፍሰጡር እናቶች መኾናቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በ2017 በጀት ዓመት በኅብረተሰቡ ውስጥ የተከሰቱ የጤና ችግሮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሢሠራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህ መካከል የወባ በሽታ አንዱ ሲኾን በመከላከል እና ሕክምናው ላይ ሰፊ ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ የወባ በሽታ ተጠቂዎችን ሕክምና ለመስጠት ግብዓት ማድረስ እና የሕክምና ሥራ እንዲሠራ በማድረግ በኩል ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በቀጣይ በ2018 በጀት ዓመት ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠሩባቸውን ጉዳዮች አንስተዋል፡፡

የኅብረተሰብ ጤና ችግር የኾኑ ወባ፣ የማኅበራዊ፣ ሥነ-ልቦና ጤና እና ከምግብ ብክለት ጋር ተያይዞ በሚመጡ በሽታዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ አመላክተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የእንስሳት እና የአካባቢ ጤናን መጠበቅ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በሽታዎች መድኃኒት እንዳይላመዱ ከግንዛቤ ጀምሮ እንደሚሠራም ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩ የተሳተፉት የደቡብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ እጸገነት አምላኩ የወባ በሽታን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።

አካባቢን በማጽዳት እና ኅብረተሰቡን በማስተባበር የዞኑ መሪዎች በሠሩት ቅንጅታዊ ሥራዎች በሽታውን መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየሴፍትኔት ፕሮግራም ዜጎችን ከተረጅነት ወደ አምራችነት እያሸጋገረ ነው።
Next articleየዲጅታል ግብር አሠባሠብ ሂደት ተግባራዊ እየኾነ ነው።