የሴፍትኔት ፕሮግራም ዜጎችን ከተረጅነት ወደ አምራችነት እያሸጋገረ ነው።

14

አዲስ አበባ: ሐምሌ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም አፈጻጸምን በአዳማ ከተማ ገምግሟል።

በከተሞች የሚታየውን ሥራ አጥነት እና ስር የሰደደ ድህነት ለመቀነስ በመንግሥት በኩል ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ተነድፎ ወደ ሥራ ተገብቷል። ከነዚህ መካከልም የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም አንዱ ነው።

የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን በ2009 ዓ.ም በ11 ከተሞች የተጀመረው የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም አሁን ላይ በ88 ከተሞች ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በእነዚህ ከተሞችም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ነው ያነሱት።

በከተሞች ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው ይህ የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሀብት አፍርተው ኑሯቸውን እንዲደጉሙ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ ሚናው የጎላ መኾኑን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።

ፕሮግራሙ በከተሞች ዜጎች የምግብ ዋስትናቸውን በሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች ተሳትፈው የራሳቸው ገቢ እንዲኖራቸው ከማድረግ በተጨማሪ የሥራ ባሕላቸውን በመቀየር፣ የቁጠባ ባሕል በማጎልበት፣ ኑሯቸውን በማሻሻል እና የከተሞችን ገጽታ በመገንባታ ረገድ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።

በ2017 በጀት ዓመት በሀገሪቱ በሁሉም ክልሎች በተመረጡ 88 ከተሞች ከ699 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በተለያዩ የልማት ሥራዎች በማሳተፍ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት ዜጎችን ከተረጅነት ወደ አምራችነት በማሸጋገር አበረታች ውጤት መመዝገቡን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የተናገሩት።

በ2018 በጀት ዓመት የዜጎችን የበለጠ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ በማድረግ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በግምገማ መድረኩ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የሥራ ኀላፊዎች፣ የክልል ቢሮ መሪዎች፣ የከተማ ከንቲባዎች እና የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ: ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየዓለም የጡት ማጥባት ሳምንት በክልል ደረጃ እየተከበረ ነው።
Next articleበኅብረተሰቡ ውስጥ የተከሰቱ የጤና ችግሮች ላይ ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል፡፡