
ጎንደር፡ ሐምሌ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የለውጥ ምክር ቤት ጉባኤ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።
በጉባኤው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አሥራት አጸደወይን (ዶ.ር) እንኳን ወደ ሰላሙ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሰላም መጣችሁ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የለውጥ ምክር ቤት ጉባኤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ እና የአጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የ100ኛ ዓመት በሚከበርበት ወቅት መካሄዱ ልዩ ድምቀት ኾኗል ነው ያሉት። ተቋሙ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጉባኤው እንዲካሄድ በማድረጉ አመሥግነዋል።
ዩኒቨርሲቲዎችን የራስ ገዝ ለማድረግ የሚካሄደው ለውጥ የሚደነቅ መኾኑን አንስተዋል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአዲስ አሠራር እና የለውጥ ሐዋርያ ናቸውም ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት አንስቶ አሁን እስከ ደረሰበት የምርምር ተቋምነት ያከናወናቸውን ተግባራት ለተሳታፊዎች አስቃኝተዋል።
ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራትን ለማምጣት የተለያዩ ተግባራትን በትኩረት እያከናወነ መኾኑንም ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ዓለማቀፋዊ ጠባይ እንዳላቸው እና በትብብር እንደሚሠሩም አንስተዋል። በኢትዮጵያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተለያዩ ምርምሮችን እና ተግባራትን በትብብር መሥራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ልምድ መቅሰሙን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው እያከናወናቸው ያሉትን ኩነቶች በመጥቀስ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተሞክሮ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ ጎንደር ከተማ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ትልቅ ድርሻ መወጣቷን አንስተዋል። አሁን ላይ የዘመናዊ ትምህርት ተደራሽነት ጥሩ ቢኾንም የጥራት ችግር እየፈተነ መኾኑን ጠቁመዋል።
የትምህርት ጥራት ማሻሻያዎች እና ምቹ የመማሪያ ክፍሎች እንዲኖሩ መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል።
በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን ያነሱት ምክትል ከንቲባዋ የትምህርት ተቋማት መውደማቸውን ገልጸዋል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር ጉባኤውን በጎንደር ከተማ በማድረጉ አመሥግነዋል። ከተማ አሥተዳደሩ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቅርበት እየሠራ ከሌሎች አካባቢዎች የሚመጡ ተማሪዎችን በቃል ኪዳን ቤተሰብ በመቀበል አብሮነትን እያስቀጠለ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ ኮራ ጡሸኔ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና የአጠቃላይ ትምህርት ተቋማት ለኢትዮጵያ እድገት ተስፋ ሰጭ መኾናቸውን አንስተዋል።
ለሁለት ቀን በሚቆየው ጉባኤ ለትምህርት ተደራሽነት፣ ለጥራት ተገቢነት፣ ውጤታማነት እና ቀልጣፋነት በትኩረት ለመሥራት ውይይት እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
በቀጣይ ለትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት ትኩረት በመስጠት መሥራት ይገባል ብለዋል።
“የትምህርት ጥራት የምርጫ ጉዳይ ሳይኾን ግዴታ ነው” ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥር እና ጥራት ሲጨምር የማኅበራዊ ፍትሕን ማስፈን እንደሚቻል አንስተዋል።
በመርሐ ግብሩ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች፣ ምክትል ፕሬዝዳንቶች፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት እና ቴክኖሎጅ ቋሚ ኮሚቴ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው ሌሎች አካላትም ተገኝተዋል።
ዘጋቢ :- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን