
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባሕር ዳር ዲስትሪክት ኀላፊዎች እና ሠራተኞች ችግኝ ተክለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባሕር ዳር ዲስትሪክት ዳይሬክተር ደሞዜ ባልቢ እንዳሉት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንደ ሀገር ከተጀመረ ጀምሮ የዲስትሪክቱ ሠራተኞች በየዓመቱ እስከ 20 ሺህ ችግኞችን ይተክላሉ። የጽድቀት ምጣኔያቸውንም የክትትል ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመትም ዲስትሪክቱ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ የችግኝ ተከላ እያካሄደ ነው ብለዋል። ሀገር በቀል እና የፍራፍሬ ችግኞች ላይ ትኩረት መደረጉንም ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሥራ እድል ከመፍጠር፣ ሥርዓተ ምግብን ከማስተካከል ባለፈ ሥነ ምኅዳርን በማስተካከል እና በረሃማነትን በመከላከል ሚናው ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል። አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከወቅታዊነት የተከላ ሥራ ባለፈ እንክብካቤ እና ጥበቃ ላይ ትኩረት ሠጥቶ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ሥራ አሥኪያጅ ባሕል ይኸይስ የዲስትሪክቱ ሠራተኞች በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የራሳቸውን አሻራ እያሳረፉ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በተቋማት እየተከናወነ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሀገሪቱ በምግብ ራስን ለመቻል እና ለአየር ንብረት ለውጥ የሰጠችው ትኩረት የሚያጠናክር መኾኑን ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ባሕል ኾኖ እንዲቀጥል ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ መሠራት እንዳለበትም አንስተዋል።
በዲስትሪክቱ የወለድ ነጻ ባንክ አገልግሎት ሥራ አሥኪያጅ ምስጋናው ከማል በየዓመቱ በችግኝ ተከላ መሳተፋቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ውጤት እንዲያመጣ የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ ላይ ትኩረት መስጥት ይገባል ብለዋል። በየዓመቱም እንደ ተከላ መርሐ ግብሩ የጽድቀት ምጣኔውን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!