
ደብረ ማርቆስ: ሐምሌ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን የአማኑኤል ከተማ አሥተዳደር በተጠናቀቀው 2017 በጀት ዓመት የተገነቡ እና ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።
የአማኑኤል ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሽታሑን የሻነህ ከተማዋን ውብ እና ምቹ ለማድረግ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ድጋፍ እና ክትትል ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በጸጥታ ችግር ውስጥም ኾኖ የከተማው ሕዝብ የሚያነሳውን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ የታየው ቁርጠኝነት የሚበረታታ መኾኑንም አንስተዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ሙሉቀን ቢያድግልኝ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸው ጀምሮ የመጨረስ ባሕልን ያሳደገ እና በፈተናም ውስጥ ኾኖ የመፈጸም አቅምን ያሳየ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ ገዳሙ መኮንን ለአገልግሎት የበቁ የመሠረተ ልማት ሥራዎች የከተማውን ሕዝብ ተጠቃሚነት በእጅጉ የሚያሳድጉ መኾናቸው ገልጸዋል። “የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ ኅብረተሰቡ ተገቢውን ጥበቃ ሊያደርግ እንደሚገባም” አስገንዝበዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎችም የረዥም ጊዜ ጥያቄያቸው መመለሱን አመስግነዋል። የተገነቡ የልማት ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡
በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ የምስራቅ ጎጃም ዞን፣ የማቻከል ወረዳ እና የአማኑኤል ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እንዲኹም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን