
ጎንደር: ሐምሌ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
የቆሻሻ ማጣሪያ፣ የሰው ሠራሽ እግር ማምረቻ፣ ኦክስጂን ማምረቻ፣ የካንሰር ሕክምና ማዕከል፣ የግቢ ማስዋብ ሥራን ጨምሮ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ነው የተመለከቱት።
ጉብኝቱ በዩኒቨርሲቲው እየተሠሩ ያሉ ሥዎችን ለማወቅ እድል እንደፈጠረላቸው የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተናግረዋል። ከዚህ በፊት ከሀገር ውጭ ይሰጡ የነበሩ ሕክምናዎችን ጨምሮ የነዋሪዎችን ጤና የሚጠብቁ ሥራዎች በዩኒቨርሲቲ ሲሠሩ መመልከታቸውን ገልጸዋል።
የተሠሩ ሥራዎችን መመልከታቸው በሆስፒታሉ ውስጥ ማገዝ የሚገባቸውን እና የድርሻቸውን እንዲወጡ እንደሚረዳ አብራርተዋል።
የጎንደር ከተማ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ስለሽ መሥፍን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኦክስጂን ማምረቻ፣ የዩኒቨርሲቲው የቆሻሻ ማጣሪያ እና ሌሎች የተሠሩ ሥራዎች ከዚህ በፊት በከተማው ነዋሪዎች ይጠየቁ የነበሩ ጥያቄዎችን ምላሽ የሰጡ ናቸው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው እና ማኅበረሰቡ የማይነጣጠሉ በመኾናቸው አስፈላጊውን ድጋፍ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቅሰዋል።
ምክትል አፈ ጉባኤው አገልግሎት አሰጣጡ የተሻለ እንዲኾን በቀጣይ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አሥራት አጸደወይን(ዶ.ር) ጉብኝት የተደረገባቸው 20 የመሠረተ ልማት ሥራዎች በዚህ ዓመት ተመርቀው ወደ ሥራ የገቡ መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ አካባቢዎች የማኅበረሰቡን ሕይወት የሚቀይሩ ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ዘጋቢ:- ዳንኤል ወርቄ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን