
ባሕር ዳር: ሐምሌ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎጃም ዞን መርዓዊ ከተማ አሥተዳድር ልዩ ልዩ ሰው ተኮር የመሠረተ ልማት ሥራዎች ተገንብተው እና ዕድሳት ተደርጎላቸው ዛሬ ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።
የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን የሜጫ ምድር በሁሉም የግብርና ዘርፍ በምርታማነት እንደሚታወቅ ጠቅሰው በተለይም የአቦካዶ ምርትን ወደ ውጭ ሀገር በመላክ በዘርፉ ለክልሉ ዐይን ገላጭ መኾኑን አስታውሰዋል።
ዞኑ እንደ ክልል የገጠመውን ችግር በመቋቋም እና ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር የሕዝቡን ዋነኛ የልማት ጥያቄ እየመለሰ ይገኛል ነው ያሉት።
ዛሬ በከተማዋ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የኾኑት ልዩ ልዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችም የእዚሁ አካል መገለጫዎች ናቸው ነው ያሉት።
እንደ ክልል ባጋጠመው የሰላም እጦት በመርዓዊ ከተማ የሕዝብ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ወድመዋል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በተለይ ወድ የኾነው የሰው ልጅ ሕይዎት ጠፍቷል ብለዋል። የዜጎች እና የመንግሥት ሃብት እና ንብረት ወድሟል።
እንደ ክልል እና ዞን ከሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ከጥምር ጦሩ ጋር በመኾን በአካባቢው ሰላምን በማስፈን የተጀመሩ እና አዳዲስ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ መቻሉን አቶ አሰፋ ተናግረዋል።
“የሕዝቡ ዋነኛ ጥያቄ መልማት በመኾኑ መንግሥት ከሕዝብ ጋር በመኾን በአንድ እጁ ሕግ እያስከበረ በሌላው እጁ ለልማት ጥያቄዎች መልስ እየሰጠ ይገኛል ነው ያሉት። ዛሬ የተመረቁት የመሠረተ ልማት ሥራዎችም የእዚሁ አካል መገለጫዎች ናቸው፤ ይህም የገጠመንን ፈተና ወደ ዕድል የመቀየር አብነቶች ናቸው” ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው።
የመርዓዊ ከተማ አሥተዳደር ከተማ ከንቲባ ብርሃኑ አበረ በበኩላቸው በ62 ሚሊዮን ብር ውጭ ልዩ ልዩ ሰው ተኮር የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን በማደስ እና በአዲስ በመገንባትም ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
ለአገልግሎት ክፍት ከተደረጉት ተቋማት መካከል የገቢዎች፣ የፖሊስ፣ የከንቲባ እና የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እና በመናኽሪያ ውስጥ የሚገኝ የመጸዳጂያ ቤት ግንባታ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
በተጨማሪም በከተማዋ አምስት የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመሮችን በመትከል 662 ግለሰቦች የኤሌክትሪክ ቆጣሪ እንዲያገኙ መደረጋቸውን ነው ከንቲባው የገለጹት።
የከተማዋ ነዋሪዎችም የሰላም እጦቱ የፈጠረው ጉዳት ዘርፈ ብዙ መኾኑን ጠቅሰው ለአካባቢው ሰላም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል። በመሠረተ ልማት ሥራዎቹ የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ በመኾናቸው ደስታቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም ዘመናዊ የመድኃኒት ቤት እና አዳራሽ ለመገንባት የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን የእለቱ የክብር እንግዶች አረጋግጠዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!