አልማ በራስ አቅም መልማት እንደሚቻል ያሳየ እና የይቻላል ስሜትን የፈጠረ ተቋም ነው።

17

ደብረ ማርቆስ፡ ሐምሌ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ልማት ማኅበር የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር (አልማ) ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጻም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) በራስ አቅም መልማት እንደሚቻል ያሳየ እና የይቻላል ስሜትን የፈጠረ ተቋም መኾኑን አመላክተዋል።

በ2017 በጀት ዓመት አበረታች ተግባራት መከናዎናቸውን ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው
የተሻለ ለመፈጸም ጉድለቶችን እየሞሉ መሄድ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የአማራ ልማት ማኅበር ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ አየነው መኮንን አልማ ከአጋር አካላት፣ ከመንግሥት እና ከአባላት ሃብት በመሠብሠብ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል ያስቻሉ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ፣ የጤና ጣቢያ ማሻሻል እና የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ሼዶችን በመገንባት አበረታች ተግባራት መፈጸሙን ተናግረዋል።

ከ2012 እስከ 2017 ባሉት ዓመታት ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ መሠብሠቡን የተናገሩት ሥራ አሥኪያጁ ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው ትምህርት ቤቶች እና ሁለት ሼዶች ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸውን አብራርተዋል።

የጸጥታ ችግሩ ካሳደረው ተጽዕኖ በተጨማሪ በፈፃሚ አካላት ላይ የሚታየው የአፈጻጸም ልዩነት እና መሰል ምክንያቶች በታቀደው ልክ ሃብት ለመሠብሠብ እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

ክፍተቶችን በመሙላት እና አስፈላጊውን የግንዛቤ ማስፋት ሥራዎች በመሥራት በ2018 በጀት ዓመት ተግባራትን በውጤታማነት ለመፈፀም መትጋት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ሀሳባቸውን የሰጡ የቀበሌ መሪዎች ማኅበረሰቡ የሚያዋጣው ገንዘብ መልሶ ራሱ ለሚጠቀምባቸው ማኅበራዊ መገልገያ ተቋማት ግንባታ እና ግብዓት ለማሟላት የሚውል መኾኑን ገልጸዋል።

የታቀደውን ሃብት በመሠብሠብ ኅብረተሰቡን የሚጠቅሙ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ሁሉም ተቋማት በቁርጠኝነት እንዲሠሩም ጠይቀዋል።

በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ባለድርሻ አካላት እና ተቋማት የዕውቅና እና የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየቴክኖሎጅ ዕውቀት እና ክህሎቶችን በማውጣት ወደተጨባጭ ሀብት መቀየር ይገባል።
Next articleበመርዓዊ ከተማ ሰው ተኮር የመሠረተ ልማት ሥራዎች ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።