የቴክኖሎጅ ዕውቀት እና ክህሎቶችን በማውጣት ወደተጨባጭ ሀብት መቀየር ይገባል።

11

ባሕር ዳር: ሐምሌ26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ከአማራ ልማት ማኅበር እና ከቤጃይ ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያል ሶሉዩሽን ጋር በመተባበር የክልሉን ወጣቶች የቴክኖሎጂ አቅም ለማሳደግ አላማ ያደረገ ሥልጠና እየሰጠ ነው።

ሥልጠናው በባሕር ዳር ከተማ እና በክልሉ ሌሎች የዞን ከተሞችም በቨርችዋል ቴክኖለጂ ነው እየተሰጠ ያለው።

የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖለጅ ቢሮ ምክትል ኀላፊ የቻለ ይግዛው እንደገለጹት ከ1 ሺህ በላይ ወጣቶች በሥልጠናው እየተሳተፋ ነው። በክልሉ ትልቅ የቴክኖሎጅ ክሕሎት እንዳለ የገለጹት ምክትል ኀላፊው ይህንን አቅም አውጥቶ ለገበያ የማቅረብ እና ወደተግባር የመቀየር ውስንነት ግን መኖሩን ጠቁመዋል። የዛሬው ሥልጠናም ወጣቶችን የሚያነቃ እና የቴክኖሎጅ ውጥኖችን አሳድጎ ሕዝብን ወደሚጠቅም ተግባራዊ ሥራ የሚያስገባ እንደሚኾን ገልጸዋል ።

ሀሳቡ በመንግሥት እና የፈጠራ ሀሳብ ባላቸው ሰዎች ተግባራዊ እንደሚደረግም ተናግረዋል። አንድ ሰው የፈጠራ ሀሳብ ስላለው ብቻ በቀላሉ ወደተግባር ሊቀይረው አይችልም፤ ይልቁንም በትብብር እና በቅንጅት በመሥራት ከዳር ማድረስ ያስፈልጋል ነው ያሉት ።

የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖለጅ ቢሮ በቀጣይ ከግለሰቦች እና ከመንግሥት ተቋማት ባሻገር ከግል ድርጅቶች ጋር በመተባበር የፈጠራ ሀሳቦችን በተግባር ለመተርጎም በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

የአማራ ልማት ማኅበር የስትራቴጅ እና ኢኖቬሽን ምክትል ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አበረ መኩሪያ ሥልጠናው በሦስትዮሽ ስምምነት እየተሰጠ እንደሆነ ተናግረዋል። ሦስቱ ተቋማት ወጣቶችን ለማብቃት የሦስት ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ ማዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል። የዛሬው ሥልጠና ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ጅማሮ መሆኑን ነው የጠቀሱት።

በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶችን ለማሠልጠን ሦስቱ ድርጅቶች በጋራ እየሠሩ እንደሆነም ገልጸዋል። የተዳፈነ የቴክኖሎጅ አቅም እና ችሎታ ያላቸው ብዙ ሰዎች አሉ፤ ይህንን የተዳፈነ አቅምና ችሎታ በማውጣት ወደተጨባጭ ሃብት ልንቀይረው ይገባል ነው ያሉት። የዛሬው ሥልጠናም አቅም እና ችሎታን ወደ ሃብት ለመለወጥ የሚያገለግል ነው ብለዋል።

አማራ ልማት ማኅበር በቅርቡ ከወጣቶች ጋር የተያያዘ ትልቅ ፕሮጄክት እንደሚያስተዋውቅም ጠቁመዋል። በቀጣይ ከ67 ሺህ በላይ ወጣት ሴቶችን እና አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ ይሠራል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየገንዳ ውኃ ከተማ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ።
Next articleአልማ በራስ አቅም መልማት እንደሚቻል ያሳየ እና የይቻላል ስሜትን የፈጠረ ተቋም ነው።