
ገንዳ ውኃ፡ ሐምሌ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ በተለያዩ ሙያዎች ያሠለጠናቸውን 88 ተማሪዎች ለ16ኛ ጊዜ አስመርቋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ ዲን አዲሱ ጫኔ ኮሌጁ ከተመሠረተ ጀምሮ ብቁ የሰው ኀይል በማፍራት በዞኑ ላሉት ኢንዱስትሪዎች መጋቢ በመኾን የድርሻውን እየተወጣ ነው ብለዋል።
ኮሌጁ በመደበኛ እና አጫጭር ሥልጠናዎችን በመስጠት 88 ተማሪዎችን በተለያየ የሙያ መስክ ብቁ አድርጎ ለምርቃ ማብቃቱንም ገልጸዋል።
ከቴክኖሎጂ ጋር የተግባባ ትውልድ ማፍራት ከቀለም ዕውቀት ባሻገር በቴክኒካል ክህሎት እጁ የተፍታታ ተወዳዳሪ ዜጋ መፍጠር የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ሥልጠና የመጀመሪያ ተግባሩ መኾኑንም አመላክተዋል።
ኮሌጁ የተለያዩ ዘመናዊ ማሽኖችን እና ስታንዳርዱ በሚጠብቀው መሠረት ወርክ ሾፖችን እየገነባ ነው ብለዋል።
በቀጣይ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጁን ወደ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
“ተመራቂ ተማሪዎች የዛሬዋን ቀን የጉዟቹሁ መጀመሪያ እና ለነገዋ የኑሯቹሁ የስኬት ጎዳና የምትጠርጉበት ለላቀ ውጤት የምታቅዱበት እንጅ መጨረሻ እንዳልኾነ መገንዘብ አለባችሁ” ነው ያሉት።
ተማሪዎች በሠለጠኑበት ሙያ ሥራ ፈጣሪ እንጅ ሥራ ጠባቂ እንዳይኾኑ አሳስበዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አብዱልከሪም ሙሐመድ ተማሪዎች በሥልጠና ያገኙትን ዕውቀት ተጠቅመው ሀገራቸውን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ በማድረግ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ተማሪዎች ሥራ በመፍጠር ያስተማራቸውን ማኅበረሰብ ማገልገል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እንዳለው ማሩ ለአንድ ሀገር ትልቁ ሃብት የተማረ የሰው ሃብት መኾኑን ገልጸዋል። የሰው ሃብትን ደግሞ ለማፍራት አይነተኛውን ድርሻ የሚይዘው ትምህርት እንደኾነ አመላክተዋል።
የሙያ ትምህርት የማይነጥፍ ሃብት እና ውጤታማ የሚያደርግ መኾኑኑም ተናግረዋል። የሙያ ትምህርት የተማረ ሰው ለራሱ ሥራ ፈጥሮ ሌሎችን የሙያ ባለቤት እንዲኾኑ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ተማሪዎች ለምረቃ በመብቃታቸው ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል። በተማሩበት ሙያም ሕዝብን እና ሀገርን ለማገልገል ዝግጁ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
በተማሩበት ትምህርትም ሥራ በመፍጠር ሌሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩም ጠቁመዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን