የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መሠረት የኾኑ ገበሬዎች በታሪክ ሲዘከሩ ይኖራሉ።

12

ጎንደር፡ ሐምሌ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲውን 70ኛ እና የአጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉን 100ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የገበሬዎችን ቀን አክብሯል።

መርሐ ግብሩ ገበሬዎች የሚመሠገኑበት፣ የሥራ ሂደታቸውን የሚገመግሙበት እና በቀጣይ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቅርበት ለመሥራት የሚወያዩበት ቀን መኾኑ ተጠቁሟል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አሥራት አጸደወይን (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው ተቋም ኾኖ ከመመሥረቱ በፊት አካባቢው የገበሬዎች የእርሻ ቦታ እንደነበር አንስተዋል።

ዘመናዊ ትምህርት ቤት ባልነበረበት እና ከመንግሥት ብቻ በሚጠበቅበት ወቅት አርቆ አሳቢ የኾኑ 59 አርሶ አደሮች ሐምሌ 11/1961 ዓ.ም የመሬት ይዞታቸውን በመልቀቅ ለዩኒቨርሲቲው አበርክተዋል ብለዋል።

ከገበሬዎች በተጨማሪ ማኅበረሰቡ ዩኒቨርሲቲውን ለመገንባት የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን አንስተዋል።

የባለ ራዕይ ገበሬዎቹ ሥራ ውጤት አፍርቶ ዩኒቨርሲቲው በመሠራቱ ከ110ሺህ በላይ ምሁራንን ማፍራት እንደተቻለ ተጠቅሷል። ተቋሙ አሁን ላለበት ደረጃ እንዲደርስ ላደረጉ ገበሬዎችም ምሥጋና አቅርበዋል።

ለዩኒቨርሲቲው የመሬት ይዞታቸውን በመስጠት ዛሬ ላይ ለደረሰበት መሠረት የኾኑ ገበሬዎች በታሪክ ሲዘከሩ እንደሚኖሩም ጠቁመዋል።

መሬት በማከም፤ ምርጥ ዘር በማሟላት፤ ቴክኖሎጅን በማቅረብ ለገበሬዎች ዩኒቨርሲቲው ድጋፍ አድርጓል፣ ይህ በቂ ባለመኾኑ የገበሬዎችን ሕይወት ለመቀየር በቀጣይም በቁርጠኝነት እንሠራለን ብለዋል።

በአካባቢው የሰሊጥ፣ ዓሳ እና ሌሎች ምርቶቾች መኖራቸውን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ በቂ ቴክኖሎጅ ባለመኖሩ የአመጋገብ ሥርዓትን መቀየር እንዳልተቻለ አንስተዋል።

የአመጋገብ ሥርዓትን በመቀየር፤ የቴክኖሎጅ አቅርቦትን በማሟላት ምርታማነትን ለማሳደግ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

በቴክኖሎጅ አቅርቦት፣ በጥናትና ምርምር፣ በሰብል ልማት፣ በእንሥሳት ሃብት፣ በምርጥ ዘር አቅርቦት እና በሌሎች ዘርፎች ገበሬዎችን ለማገዝ በቁርጠኝነት እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ በምግብ ራስን ለመቻል ቴክኖሎጅን ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በዞኑ የገበሬዎችን ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ በቴክኖሎጅ አቅርቦት እየደገፈ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ለገበሬዎች ለውጥ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታ ያላቸው ተግባራትን በማከናወን ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግእያደረገ ላለው ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል።

ዞኑ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቀጣይ በቅርበት እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ገበሬዎች ዩኒቨርሲቲው በምርጥ ዘር፣ በቴክኖሎጅ፣ በእንሥሳት ሃብት እና በተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ እያደረገላቸው መኾኑን አንስተዋል። ለሚያደርገው ድጋፍም አመሥግነዋል።

ዩኒቨርሲቲው ባደረገላቸው ሙያዊ ድጋፍ እና ሥልጠና ሕይዎታቸው እየተቀየረ መምጣቱንም ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ፦

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሥልጠናው ወጣቶች ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርሱ የሚያነሳሳ ነው።
Next articleየገንዳ ውኃ ከተማ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ።