ሥልጠናው ወጣቶች ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርሱ የሚያነሳሳ ነው።

14

ጎንደር፡ ሐምሌ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከጎንደር ከተማ፣ ከማዕከላዊ እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የተወጣጡ ወጣቶች እምቅ ችሎታቸውን ተጠቅመው ከራሳቸው አልፈው ለሀገር የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጡ የሚያስችል ሥልጠና እየወሰዱ ነው።

ሥልጠናውን ቢጅ አይ ኢትዮጵያ፣ የአማራ ክልል የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ እና የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) በጋራ ያዘጋጁት ነው። ሥልጠናው በዙም የመገናኛ አውታር ታግዞ ነው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እየተሰጠ የሚገኘው።

የሥራ ፈጠራ ሂደትን ለማነቃቃት ታስቦ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እየተሰጠ ባለው የክህሎት ሥልጠና በአጠቃላይ 150 ወጣቶች ተሳታፊ መኾናቸውን የጎንደር እና አካባቢው አልማ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደረጀ ዘውዴ ተናግረዋል።

ወጣቶች ያላቸውን ችሎታ ከወቅቱ የቴክኖሎጅ ዕድገት እና ከወቅታዊ ማኅበራዊ ለውጦች ጋር በማጣመር የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ የሚያስችል መኾኑ ተነስቷል።

የጎንደር ከተማ አልማ ጽሕፈት ቤት ዳሬክተር ይላቅ ዓለምሰገድ የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ከሚሠራቸው በርካታ ተግባራት መካከል ወጣቶች የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያዳብሩ ማገዝ አንዱ መኾኑን ተናግረዋል።

ወጣቶች ያላቸውን ችሎታ መሠረት ያደረገ የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ተቋማቸው በትኩረት እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

የወጣቶች ቴክኖሎጅ ነክ የፈጠራ ውጤቶች ማኅበራዊ ይዘት እንዲኖራቸው በማድረግ አዳዲስ እሳቤዎችን እና የፈጠራ ሥራዎችን እንዲያመነጩ ተከታታይ ድጋፍ እንደሚሰጥም አመላክተዋል።

በሥልጠናው እየተሳተፉ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል ወጣት ናርዶስ ኤልያስ ለአሚኮ እንዳለችው ሥልጠናው የአስተሳሰብ አድማስን የሚያሰፋ፣ ወጣቶችን ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርሱ የሚያነሳሳ ነው።

ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምዕራብ ደንቢያ ወረዳ የመጣው ወጣት ብርሃኑ ሲሰጥ ሥልጠናው ያላቸውን የንድፈ ሃሳብ ዕውቀት ወደ ገንዘብ ለውጠው ከራሳቸው አልፈው የሌሎች ሰዎችን ሕይዎት መቀየር የቻሉ ወጣት ባለሃብቶች ተሞክሮ መቅረቡ አስተማሪ መኾኑን ተናግሯል።

ዘጋቢ፦ ኃይሉ ማሞ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article445 ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ መቻሉን የሰሜን ወሎ ዞን አስታወቀ።
Next articleየጎንደር ዩኒቨርሲቲ መሠረት የኾኑ ገበሬዎች በታሪክ ሲዘከሩ ይኖራሉ።