
ወልድያ፡ ሐምሌ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በወቅታዊ የሰላም እና የልማት ሥራዎች ዙሪያ ከአማራ ሚዲያ ኮርፓሬሽን ጋር ቆይታ ያደረጉት የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር በዞኑ በርካታ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል።
የተከሰተው የጸጥታ ችግር የዞኑን ነዋሪዎች ማኅበራዊ እረፍት ከመንሳት ባሻገር የተለያዩ የልማት ሥራዎች እንዳይፈፀሙ እክል ፈጥሮ ቆይቷል ነው ያሉት።
ግጭትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተደረጉ ተደጋጋሚ ሕዝባዊ ምክክሮች አሁን ለተገኘው አንጻራዊ ሰላም የላቀ አስተዋጽኦ ነበራቸው ብለዋል።
እስከ ቀበሌ ድረስ ከፍተኛ መሪዎች የተሳተፉባቸው መድረኮች በስፋት መካሄዳቸውን ያነሱት ዋና አሥተዳዳሪው የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ከ2ሺህ በላይ የታጠቁ ኀይሎች ወደ ሕዝባቸው መቀላቀላቸውን ጠቁመዋል።
የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለተገኘው አንጻራዊ ሰላም የላቀ አበርክቶ እንደነበራቸውም ገልጸዋል።
የመንገድ፣ የውኃ፣ የመስኖ፣ የትምህርት፣ የጤና ተቋማት ግንባታ እና የግብርና ሥራዎችን በ2017 በጀት ዓመት በትኩረት እና በውጤታማነት መፈጸም መቻሉንም ገልጸዋል።
በከተሞች የኮሪደር ልማት ሥራን ጨምሮ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በትኩረት መከናዎናቸውንም አንስተዋል።
“የጸጥታ ችግሩ ፈታኝ የነበረ ቢኾንም ከሰላም ማስፈን ሥራዎች 445 ፕሮጀክቶችን መሥራት ተችሏል” ብለዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በዞኑ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ 633 ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ ታቅዶ 445 ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን እና 122ቱ ፕሮጀክቶች በሥራ ላይ እንደኾኑ ገልጸዋል፡፡
የዞኑን ሰላም በዘላቂነት ለመመለስ እየተሠራ መኾኑን የተናገሩት አሥተዳዳሪው ኅብረተሰቡ የሰላሙ ባለቤት እየኾነ መምጣቱንም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን