
ባሕር ዳር: ሐምሌ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከዞን እና ከወረዳ ለተውጣጡ ሴት የሥራ ኅላፊዎች እና እጩ ሴት መሪዎች በባሕር ዳር ከተማ ሥልጠና እየሰጠ ነው።
ሥልጠናው የሴቶችን የመሪነት ብቃት ማዳበር እና ማሳደግ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። ሥልጠናውን የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከዩኤን ውመን ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጁት።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ አሁን ሥልጠና የምትወስዱ ሴቶች መሪነት ፈተና በኾነበት እና ብዙ ድጋፍ በሚጠየቅበት ወቅት የተገኛችሁ በመኾናችሁ ጀግናዎች ናችሁ ብለዋል።
ከሥልጠናው በኋላ የበለጠ የመሪነት አቅማችሁን አዳብራችሁ ለብዙ ሴቶች ተስፋ እንደምትኾኑ አምናለሁ ነው ያሉት።
መሪ ስንኾን ብዙ ኀላፊነት አለብን፤ ኀላፊነታችንን ተጠቅመን ከኛ የተሻሉ ሀገርን ሊያሻግሩ የሚችሉ እና ዕድሉን ባለማግኘታቸው ጎልተው ያልወጡ ሴቶችን ማሰብ እና ወደፊት እንዲመጡ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥርዓተ ጾታ እኩልነት የአማራ ክልል ማሥተባበሪያ ፕሮግራም ኦፊሠር ደሳለው አለኸኝ ለሴት መሪዎች እየተሰጠ ያለው ሥልጠና የሴቶችን መሪነት ሚና ለማጎልበት እንደኾነ ተናግረዋል። በቀውስ ወቅት ከችግር የሚወጣበትን መንገድ ተረድተው መምራት እንዲችሉ ለማስቻል መኾኑንም ገልጸዋል።
አኹን ያለንበት ወቅት የቀውስ ጊዜ ነው ያሉት አቶ ደሳለው ከዚህ ችግር ለመውጣትም ለሴት መሪዎች ሥልጠና መሠጠቱ ተጨማሪ አቅም ይኾናል ነው ያሉት።
ከሥልጠና በኋላም ሴት መሪዎች ከነበረባቸው ማኅበራዊ ጫና ተላቀው የበቁ መሪዎች እንዲኾኑ የተሠጣቸውን ሥልጠና መተግበር ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ዘጋቢ: ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን