
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አካል ጉዳተኞች በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች እየተሳተፉ ነው።
በባሕርዳር ከተማ የክረምት በጎ ፈቃድ ደም የመለገስ መርሐግብር “ደም በመለገስ የብዙዎችን ሕይዎት እንታደግ” በሚል መሪ መልዕክት ተካሂዷል። በዚህ የደም ልገሳ መርሐ ግብር አካል ጉዳተኞች ደማቸውን ለግሰዋል።
ወይዘሮ አንሻ ኑረዲን በመርሐግብሩ ላይ ደም ሲለግሱ አሚኮ ያገኛቸው እናት ናቸው። ደም በመለገሳቸው ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል። “ደም ለግሸ የተቸገረችን እናት እና የተጎዱ ሰዎችን ሕይወት ማትረፍ በመቻሌ ደስተኛ ነኝ” ብለዋል።
በባሕር ዳር ከተማ የአካል ጉዳተኞች ማኅበር ፌዴሬሽን ሠብሣቢ ዳንኤል አበበ በበኩላቸው አካል ጉዳተኞች በየትኛውም ቦታ ላይ እንደ ማንኛውም ጉዳት እንደሌለበት ሰው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በክረምት ወቅት በተለያዩ የበጎ ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙም አብራርተዋል። የከተማ አሥተዳደሩ በሚያዘጋጃቸው የልማት መርሐግብሮች እኩል ተሳታፊ በመኾን አካል ጉዳተኞች አይችሉም የሚለውን አመለካከት መቀየር እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ሴቶች እና ሕጻናት ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ምክትል ኀላፊ አሻገሩ አሊ አካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም ሙሉ አካል እንዳለው ሰው በሁሉም ዘርፍ ይሠራሉ፣ ተሳታፊም ናቸው ነው ያሉት።
ከዚህ በፊት በክረምት ብዙ ሥራዎችን መሥራታቸውን የተናገሩት ምክትል ኀላፊዋ በደም ልገሳ፣ በመማር ማስተማር፣ በችግኝ ተከላ፣ በቤት ጥገና፣ በጽዳት እና መሰል ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ሠርተዋል ብለዋል።
ጉዳታቸው ሳያግዳቸው አሁን ደግሞ እንደሌላው ማኅበረሰብ ደም በመለገስ ላይ እንደሚገኙም አመላክተዋል።
የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍሬሰላም ዘገየ ሕይዎት ለማስቀጠል ደም መለገስ ይገባልም ብለዋል።
ደም ለሚፈሳቸው እናቶች፣ ሕጻናት እና አደጋ ለገጠማቸው ሰዎች አካል ጉዳተኞች ደም በመለገስ አጋርነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባቸውም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ ሰማሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
