“የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር የኢትዮጵያን የመምራት፣ የመፍጠር እና ራሷን ለዓለም የመግለጥ ፍላጎቷ ማሳያ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

40

ባሕርዳር ፡ ሐምሌ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ሥራ ከጀመረ 130ኛ ዓመቱን ዛሬ አክብረናል ብለዋል።

በዓድዋ የድል መንፈስ የተወለደው ይህ የባቡር አገልግሎት መስመር ከብረት የተሠራ ማጓጓዣ ብቻ አይደለም – የኢትዮጵያን የመምራት፣ የመፍጠር እና ራሷን ለዓለም የመግለጥ ፍላጎቷ ማሳያም ጭምር እንጂ ነው ያሉት።

ባቡራችን አንድ ለእናቱ ሆኖ የቀረው በታሪካችን የጀመርነውን አለማጠናቀቅ እና ያለማስቀጠል ችግር ሰለባ በመሆኑ ነው። ከለውጡ ወዲህ ጀምሮ ያለመጨረስ ስብራትን ለማስወገድ “ከጀመርን ሳንጨርስ አናርፍም” በሚል መንፈስ እየተጋን ድሎችን እያስመዘገብን እንገኛለን ብለዋል።

የሀገር ዕዳ ሆኖ የቆየው የኢትዮ- ጂቡቲ ባቡር በለውጡ ዓመታት በተሰጠው ትኩረት ወደ ምንዳ በመሸጋገር ላይ ይገኛል፤ የሀገር ገቢና ወጪ ንግድ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሆኗል። ይህ አዲስ ምዕራፍ ነው፤ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ጉዞ በባቡር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስም ዕውን ሆኗል ነው ያሉት።

ቅድመ አያቶቻችን የዘመናዊነትን ፈር በመከተልም በአፍሪካ ቀዳሚ የባቡር መስመርን እውን አድርገዋል።አሁን ተራው የኛ ነው – ማለም፣ መገንባት፣ የጀመርነውን መጨረስ። ማሳበብ ሳይሆን መፈጸም። ታሪክ ማውራት ብቻ ሳይሆን ታሪክ መሥራታችንን መቀጠል ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ በግልጽ ራዕይ፣ በአንድነታችን እና በባቡር መሠረተ ልማት መስፋፋት እውን ይሆን ዘንድ መትጋት አለብን። የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር አክሲዮን ማኅበር የለውጥ መሪዎችና ሙያተኞች የተጣለባችሁን አደራ በአግባቡ እየተወጣችሁ በመሆኑ በኤፌዲሪ መንግሥት እና በራሴ ስም ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleቴክኖሎጅን ለበጎ ዓላማ።
Next articleየኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዕውቅና ሰጠ።