ቴክኖሎጅን ለበጎ ዓላማ።

17

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የማኅበራዊ ሚዲያ ቴክኖሎጂ መዘመን እና ማደግ ጋር ተያይዞ ከተለያዩ ምንጮች እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው መረጃ ይለቀቃል። ምን ያህሉ ግን ትኩረታችንን መያዝ ይችላል?

እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ2018 ዓ.ም ማይክሮሶፍት ያወጣው የጥናት ውጤት የሰው ልጅ በአንድ ይዘት ላይ ሊኖረው የሚችለው ትኩረት በ2000 ዓ.ም 12 ሴኮንድ ከነበረው ወደ 8 ሴኮንድ አሽቆልቁሏል።

በዲጀታል ዓለም የሰውን ልጅ ትኩረት ቆንጥጦ መያዝ የሚችል ይዘት ይዞ መቅረብ ፈታኝ መኾኑን ጥናቱ ያስርዳል። ይህን ሰብሮ የብዙ ሚሊዮኖችን ትኩረት አሸንፎ መውጣት የቻለ ሰው ግን በሕይዎት መንገድ ውስጥ እናገኛለን። ያውም በዲጂታሉ ዓለም።

በዓለማችን በዩቲዩብ ታሪክ ስሙ የገዘፈ ነው። ትክክለኛ ስሙ ጂሚ ዶናልድሰን ይባላል። እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ1998 ዓ.ም አሜሪካ ካንሳስ ውስጥ ነው የተወለደው።

ስሙን የሚያገዝፍ ታሪክ ይኖረዋል ብሎ የጠበቀ አልነበረም። እሱም ቢኾን በዚህ መንገድ አሰቦ አያውቅም ነበር። ገና በልጅነት ዕድሜው በኢንተርኔቱ ዓለም ዩቲዩብ ከሚባለው የቪዲዮ ገጽ ጋር እንደ ቀልድ ወዳጅነት ጀመረ። ገና በ13 ዓመቱ ነበር የዩቲዩብ ቻናል ከፍቶ በጎ ተጽዕኖ ያላቸውን ቪዲዮዎች እየሠራ ማሰራጨት የጀመረው።

ጂሚ ዶናልድሰን በሚለው መጠሪያው አብዛኛው ሰው አያውቀውም። ሰው የሚያውቀው በዩቲዩብ ስሙ በገነነበት ሚስተር ቢስት በሚል የቻናሉ መጠሪያ እንጂ።

በተከታይ ብዛት ዩቲዩብ ላይ ቁንጮ ኾኖ ዓመታትን ተሻግሯል። ከ418 ሚሊዮን በላይ የቻናሉ ተከታዮችን አፍርቷል። በቪዲዮ ሥራዎቹ ለተሳታፊዎች ትላልቅ ሽልማቶችን እና ረብጣ ገንዘብ በመስጠት ይታወቃል።

በ2017 እስከ 100ሺህ ቆጠርኩ የሚል ቪዲዮ ከሠራ በኋላ በአጭር ጊዜ ተወዳጂነትን ማትረፍ ችሏል። ከጓደኞቹ ጋር በመተባበር ቲም ትሪ እና ቲም ሲ የተባሉ የበጎ አድራጎት ፕሮጀክቶችን በማቋቋም ዛፎች እንዲተከሉ እና ውቅያኖሶች ከብክለት የጸዱ እንዲኾኑ ለማድረግ የሚያግዝ ከ53 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሠብሠብ ችሏል።

ሚስተር ቢስት በበጎ አድራጎት ሥራው የሚታወቅ ሲኾን የትርፉን ከፍተኛ ድርሻ ለበጎ አድራጎት እንደሚያውለው ግለ ታሪኩ ያስረዳል።

ቴክኖሎጂን ለበጎ ዓላማ በመጠቀም የዐይን ብርሃናቸውን ላጡ ብርሃን፣ ንጹሕ መጠጥ ውኃ ማግኘት ላልቻሉ አፍሪካውያን ጥምቆራጭ፣ ለተራቡት አጉራሽ እና ለታመሙ ሰዎች ጠያቂ እና ደጋፊ ነው።

በተለያዩ የዓለማችን ክፍል ለሚኖሩ 1ሺህ ዐይነ ሥውራን ሙሉ የቀዶ ጥገና ወጭያቸውን በመሸፈን ማየት እንዲችሉ ረድቷል። በአፍሪካ የመጠጥ ውኃ ጉድጓድ በማሠራት ለብዙኀኑ የውኃ አቅርቦት እንዲኖር አድርጓል፣ ለተራቡት የምግብ እና ጥሬ ገንዘብ ይረዳል። በልብ በሽታ ለሚስቃዩ ሕፃናት ወጭያቸውን በመሸፈን የሕክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ያግዛል።

በአፍሪካ ለጤና ተቋማት እና ትምህርት ቤት ግንባታ ብዙ ድጋፍንም አድርጎል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleጣናነሽ ቁጥር ፪ የዚህ ወቅት የኢትዮጵያውያን የአንድነት እና የአብሮነት ማሳያ ምስጢር ኾናለች።
Next article“የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር የኢትዮጵያን የመምራት፣ የመፍጠር እና ራሷን ለዓለም የመግለጥ ፍላጎቷ ማሳያ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ