
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጣናነሽ ቁጥር ፪ ባሕር ዳር ገብታለች። ባሕር ዳር ስትገባ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላታል።
በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ጣና ነሽ ፪ የእኛነታችን፣ የአንድነታችን፣ የአብሮነታችን፣ የማይደበዝዘው ኢትዮጵያዊነታችን ማሳያ ክስተት ናት ብለዋል።
ጣናነሽ ፪ ከወራት ጉዞ በኋላ ባሕር ዳር መድረሷን ገልጸዋል። በሰላም ስለደረሰችም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። “እኛ ኢትዮጵያውያን ደም እና አጥንታችን፣ ነፍስ እና ስጋችን፣ በኢትዮጵያዊነት ልዩ ውሕድ የተሠራን፣ በጽኑ የተጋመድን ድንቅ ሕዝቦች ነን” ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን የቀደምት ሥልጣኔ፣ የአኩሪ ታሪክ፣ ነጻነቷን፣ ክብሯን ጠብቃ የኖረች፣ የአፍሪካውያን የነጻነት ተምሳሌት የኾነች ሀገር ባለቤቶች ነን ነው ያሉት።
ታላቋ ሀገር ክብሯ፣ ነጻነቷ እና ታሪኳ ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የሚገኘው ኢትዮጵውያን በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ምንም የማይለያዩ በመኾናቸው ነው ብለዋል። ችግር እና ፈተና በገጠማቸው ጊዜ ሁሉ በአንድነት የሚቆሙ ብሔራዊ ጀግኖች እና አርበኞች በመኾናቸው መኾኑንም ተናግረዋል።
“በየዘመናቱ ችግር እና ፈተናዎች አጋጥመውን ያውቃሉ” ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ነገር ግን ሁሉንም ፈተናዎች አልፈናቸዋል ነው ያሉት።
ዘመን የማይሽራቸው የኢትዮጵያ ድሎች የተገኙት በውስጣችን ምንም ችግር ሳይኖር ቀርቶ ሳይኾን ኢትዮጵያዊነት ከችግሮች በላይ በመኾኑ ነው ብለዋል።
ዛሬም ከውስጥም ከውጭም ችግሮች አሉብን ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እኛ ኢትዮጵያውያን እናልፈዋለን ነው ያሉት። በአንድነት የአንድነት እና የማንሰራራት ዘመን አሻራችንን እናሳርፋለን ብለዋል።
“ጣናነሽ ፪ የዚህ ወቅት የኢትዮጵያውያን የአንድነት እና የአብሮነት ማሳያ ምስጢር ኾናለች” ነው ያሉት።
ከጅቡቲ ወደብ ተነስታ ባሕር ዳር እስከገባች ድረስ የታዩ ክስተቶች ማሳያ እንደኾኑም ገልጸዋል።
“ጣናነሽ ፪ በዘመናት ብዛት የማይደበዝዘው ኢትዮጵያዊ አንድነታችን፣ አብሮነታችን እና ፍቅራችን የተገለጸባት ናት” ብለዋል። ብርቱ፣ ጽኑ፣ ለችግር የማንበገር መኾናችን ማሳያ ኾና ብቅ ብላለች ነው ያሉት።
ለወራት በተደረገው ጉዞ አስተዋጽኦ የነበራቸው ሁሉ ጀግኖች ናቸው እና እናከብራቸዋለን ብለዋል። ጣናነሽ ፪ በደረሰችበት ሁሉ ኢትዮጵያውያን በፍቅር እየተቀበሉ በፍቅር እንደሸኟትም ገልጸዋል። ጣናነሽ ፪ የኢትዮጵያውያን ሃብት መኾኗንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንግዜም ከጎናችን እንደማይለይ ያረጋገጠበት ነው ብለዋል። የባሕርዳር ሕዝብም በድምቀት እንደተቀበላት ነው የተናገሩት።
በድምቀት ለተቀበሏት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል። በአቀባበሉ የከተማዋ ሕዝብ ልማት ፈላጊ ብቻ መኾኑን እና ባሕር ዳር ሰላም እንደኾነች አሳይቷል ነው ያሉት።
ጣናነሽ ፪ ከመነሻዋ እስከ መድረሻዋ የታየው ድንቅ ኢትዮጵያዊነት የአብሮነታችን፣ የአንድነታችን ደማቅ ምልክት እና የታሪካችን አካል ኾኖ ተመዝግቧል ብለዋል።
ጣናነሽ ፪ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ውጤት መኾኗንም ተናግረዋል። የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት እንዲዘምን የፌዴራል መንግሥት ላደረገው አስተዋጽኦም ምሥጋና አቅርበዋል።
ባሕር ዳር የቱሪዝም መዳረሻ እና የኢንቨስትመንት መናገሻ እንድትኾን እንደሚሠራም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን