
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 13ኛው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የፌዴራል እና የክልል ባለድርሻ የመንግሥት ተቋማት የጋራ ጉባዔ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
በጉባዔው መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን መኃሪ (ዶ.ር) የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለሁለንተናዊ ልማት የማይተካ ሚና እንዳላቸው ገልጸው ምቹ ኹኔታ እየተፈጠረላቸው መኾኑን ገልጸዋል።
ድርጅቶቹ ከመንግሥት ጋር በትብብር የሚሠሩበትን ኹኔታ ለማመቻቸት የምክክር መድረኮች እየተከናዉ ነውም ብለዋል።
ምቹ ኹኔታዎችን በመጠቀምም 181 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር መፈራረማቸውን ተናግረዋል። በአስቸኳይ ድጋፍ፣ ዘላቂ ልማት እና በሰላም ግንባታ ላይ ተሰማርተዋልም ብለዋል።
ባለሥልጣኑም ለጉዳት ለተጋለጡ የክልሉ አካባቢዎች የምግብ ድጋፍ ለማድረግ ላደረገው ጥረት አመስግነዋል።
ክልሉ በሰሜኑ ጦርነት እና በውስጥ ግጭት የደረሰበትን ጉዳት ለማስተካከል የመልሶ ግንባታ ሥራ እየሠራ መኾኑን ገልጸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም እንዲያግዙ ጠይቀዋል።
የጋራ ጉባዔው መልካም ሥራዎችን በማስቀጠል እጥረቶችን ለማረም ትምህርት የሚወሰድበት መኾኑንም ተናግረዋል።
የኢፌዴሪ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን ቢራቱ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እንዲያግዙ ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምቹ ምህዳር መኖሩን ጠቅሰዋል።
የድርጅቶቹን ጠቀሜታ ለማግኘትም ተግባራት እየተፈጸሙ ነው። ከአጋር አካላትም ጋር በትብብር የሚሠሩበት ስልት ተዘርግቷል ብለዋል።
ሲቪል ድርጅቶች የኢትዮጵያን ህልሞች ለማሳካት አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ጉባዔው ትኩረት እንደሚሰጠውም ገልጸዋል።
የሲቪል ማኅበራትን የእርስ በርስ ቁጥጥር ሥርዓት ለማጠናከርም እየተሠራ ነው ብለዋል። ክልሎችም ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
የፍትሕ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ የጋራ ጉባዔው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ያልተቋረጠ እና ላቅ ያለ ሚና እንዲወጡ ታስቦ እንደተዘጋጀ ተናግረዋል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለበለጸገች ኢትዮጵያ የበኩላቸውን እንዲወጡ ምቹ ኹኔታ መፈጠሩን ጠቅሰው ውጤቶችም ውስንነቶችም መኖራቸውን አንስተዋል።
በቀጣይ ዓመታትም ሚናቸውን ማሳደግ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። ለዚህም የትብብር እና ቅንጅትን አስፈላጊነት አንስተዋል።
በፌዴራል እና በክልሎች በትኩረት የሚመራ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና የባለድርሻ አካላት የትብብር መድረክ መኖሩን አንስተዋል። ሁሉም ክልሎች የቅንጅት መድረኩን በማደራጀት ለ2018 ዓ.ም ወደ ሥራ እንዲገቡ አሳስበዋል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ራስን የመቻል ግብን በመያዝ ፋይናንስን ጨምሮ ሥራዎቻቸውን ለመሥራት የሚያስፈልጓቸውን በሀገር ውስጥ አቅም ለማሟላት መሥራት የሚጠይቃቸው ላይ እንገኛለንም ብለዋል።
ሰብዓዊ ድጋፍን በውስጥ አቅም ለማቅረብ ከወዲሁ እንዲዘጋጁ እና ለዘላቂ ልማት ላይ እንዲያተኩሩ ነው ሚንስትር ዴኤታው ያሳሰቡት።
የፌዴራል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ ድርጅቶቹ ለኅብረተሰብ ተጠቃሚነት ያላቸውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የሚገመገምበት ሠድረክ መኾኑን ገልጸዋል።
የጉባዔው ተሳታፊዎች ሰላም ኢትዮጵያ እና ወንድም ካሊድ ፋውንዴሽን ድርጅቶች ጋር በመተባበር 80 ሚሊየን ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ በጉባዔው ስም ለአማራ ክልል ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን