
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት በዞኑ የወጣቶች ክንፍ አስተባባሪነት ለተቸገሩ አረጋውያን እና ተማሪዎች ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉ የተሠበሠበው ከበጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ነው።
የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን እንዳሉት ይህ ተግባር በክረምት ወራት ሊከናወን የታቀደው የበጎ አድራጎት ሥራ አካል ነው።
ድጋፉ የማኅበረሰቡን አቅም በመጠቀም ችግረኞችን በዘላቂነት ለመደገፍ እና ችግሮችን ለመፍታት ያለውን ጠቀሜታ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ማስተዋል አሰሙ የድጋፉ ዓላማ በጎነት የሀገር ወዳድነት መገለጫ እንደኾነ በማሳየት ካላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሠብሥቦ ለሌላቸው መድረስ እንደሚቻል ማሳያ መኾኑን ገልጸዋል።
በዚህ መርሐ ግብር ከሦስት ከተማ አሥተዳደሮች እና ከአንድ ወረዳ ለመጡ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ አረጋውያን የምግብ ቁሳቁስ፣ ብርድ ልብስ እና ለ50 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።
ይህንን ተግባር በማስተባበር ለተሳተፉ አካላት እና ለለጋሾችም የምሥጋና እና የዕውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።
ድጋፍ ለተደረገላቸው አረጋውያን ለተደረገላቸው ድጋፍ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን