
ደብረብርሃን፡ ሐምሌ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ የመኸር ኩታገጠም የስንዴ ሰብል የዘር ንቅናቄ መርሐግብር በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ክፍለ ከተማ ጎሸባዶ ቀበሌ አካሂዷል።
የከተማ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኀላፊ መርሻ አይሳነው በተያዘው የመኸር የምርት ዘመን በከተማ አሥተዳደሩ 22 ሺህ 630 ሄክታር መሬትን በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በዘር ከሚሸፈነው አጠቃላይ መሬት ውስጥ 7 ሺህ 441 ሄክታሩ በስንዴ ዘር ይሸፈናል ያሉት ኀላፊው ከዚህ ውስጥ 4ሺህ ሄክታሩ በኩታ ገጠም የሚሸፈን መኾኑንም ገልጸዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ በምርት ዘመኑ 814 ሺህ 690 ኩንታል ምርት ይሠበሠባል ተብሎ ይጠበቃል፤ ምርታማነትንም በአማካኝ በሄክታር 36 ኩንታል ለማድረስ ግብ ተቀምጦ እየተሠራም ነው ተብሏል።
ይሄን ለማሳካት 54 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ፣ 896 ኩንታል የምርጥ ዘር እና የአፈር አሲዳማነትን ለማከም 4 ሺህ ኩንታል ኖራ ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል። ባለሙያዎችም ማሳ ተኮር ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ታጠቅ ገድለ አማኑኤል የስንዴ ኩታገጠም አሠራር በአርሶ አደሮች ልምድ እየኾነ ይገኛል ብለዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ.ር) በ2017/18 የመኸር የምርት ዘመን በክልሉ 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በማልማት ከ187 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ እንደኾነ ገልጸዋል።
ከምርት ዘመኑ ከሚታረሰው አጠቃላይ መሬት 51 በመቶው በኩታ ገጠም የሚለማ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ለመሠብሠብ ከታሰበው አጠቃላይ ምርት ውስጥ 61 በመቶው ከኩታ ገጠም የሚገኝ መኾኑን አብራርተዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ስለሺ ሙሉነህ ስንዴን በኩታ ገጠም በመዝራት እና አሠራሮችን በማዘመን ሀገሪቱን ከድህነት እና ከተረጅነት ለማላቀቅ እየተሠሩ ባሉ ሥራዎች ለውጦች እና ውጤቶች እየተመዘገቡ መኾኑን አንስተዋል። እየታየ ያለው ለውጥም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።
አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡት የጎሸባዶ ቀበሌ አርሶ አደሮች ስንዴን በኩታ ገጠም በመዝራታቸው ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን