
ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ጣናነሽ ፪ ጀልባን ለመቀበል በጉጉት እየጠበቁ ነው።
ዘመናዊ ጀልባዋን ለመቀበል በአደባባይ የተገኙ ነዋሪዎች የጀልባዋን መቃረብ ተከትሎ ደስታቸውን ለአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ገልጸዋል።
ነዋሪዎች ባሕር ዳር እንግዶችን የምታስተናግድ፣ ጣና ሐይቅም የቱሪስት መስህብ የኾኑ በርካታ ገዳማትን የያዘ ነው፤ የጀልባዋ መምጣት ደግሞ ለዚህ ሁሉ ተጨማሪ አቅም ነው ብለዋል።
በተለይም በሐይቁ ላይ የሚገኙትን ደሴቶች እና ሃይማኖታዊ ቦታዎች እየተዘዋወሩ ለመጎብኘት የጀልባዋ መምጣት ወሳኝ ነው ብለዋል።
ከዚህ በፊት ስታገለግል የነበረችዋ ጀልባ በእድሜ የገፋች እና አንድ ብቻ በመኾኗም ለደህንነት ስጋት በኾነ መንገድ በርካታ ሰዎችን የምታስተናግድ እንደነበረችም ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ጣናነሽ ፪ መምጣቷ ነዋሪዎች እና ቱሪስቶችም ደህንነታቸው ተጠብቆ የጣና ሐይቅ ላይ ትራንስፖርት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ያስችላል ነው ያሉት።
በተለይም በርካታ ሰዎች የሚሳተፉበት የባሕር ላይ ሃይማኖታዊ ጉዞ ሲኖር ያለ እንግልት እና በሰዓቱ አገልግሎቱን ለማግኘት የጣናነሽ ፪ መምጣት ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
ጀልባዋ ከጅቡቲ ጀምራ በፍቅር ሲሸኟት ለነበሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው ባሕር ዳር የቱሪዝም ከተማ ናት፤ ጣናነሽ ፪ መምጣቷ ደግሞ በተለይም ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ የሚያነቃቃ ነው ብለዋል።
የጀልባዋ ዘመናዊነት እና ምቾት ትሰጣለች ተብሎ ከሚጠበቀው ቀልጣፋ አገልግሎት ጋር ተደማምሮ የባሕር ዳር ከተማን ቱሪስቶች የቆይታ ጊዜ ለማራዘም እንደሚረዳም ተናግረዋል።
በጣና ደሴቶች ላይ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን መጎብኘት ለሚፈልጉ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶችም ምቹ ሁኔታዎችን ትፈጥራለች ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!