
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለአንድ ሀገር መለወጥ እና መስፈንጠር የምርምር ሥራዎች ወሳኝ ናቸው። ሀገር በቴክኖሎጅ ስትመራ ተወዳዳሪ እና ቀዳሚ ትኾናለች። የሀገርን እጣ ፈንታ ሊቀይሩት የሚችሉት ደግሞ የሀገሪቱ ዜጎች ናቸው። ዜጎች ተመራማሪ እና አዲስ ሀሳብ አፍላቂ በኾኑ ቁጥር ሀገርን ማስፈንጠራቸው አይቀሬ ነው።
አሚኮ ከዚህ በፊት አንድ ሀገር ተስፋ ልትጥልበት የምትችለው የምርምር ዘገባ ዳስሶ ለተመልካችና አንባቢ አቅርቦ ነበር – ከአፈር ላይ ነዳጅ የማምረት ጥበብን።
ይህ ዘገባ አየር ላይ እንደዋለ ብዙዎቹ አድንቀውታል፤ እንዲህም ይቻላል እንዴ ብለውለትም ነበር። የዚህ የምርምር ባለቤት የያኔው ተማሪ አሁን ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ መምህር አቡሃይ ውብሸት ሀይድሮ ካርቦኑ ከፍተኛ ከኾነ ጥቁር አፈር ላይ ነዳጅ ማምረት እንደሚቻል በ2007 ዓ.ም አስተዋወቀ።
ተመራማሪው ይዞት ብቅ ያለው በሰሜን ተራራዎች አካባቢ በስፋት የሚገኝ የአፈር አይነት ላይ ነዳጅ ማምረት ነበር። የአፈሩ አይነትም ዱቤ በመባል በአካባቢው ይታወቃል። ይህ ሥራ በተግባር በተሽከርካሪዎች ላይም ተሞክሮ በትክክል ተረጋግጧል።
ለመኾኑ ይህ ሥራ ምን ደረጃ ደርሶ ይኾን?
መምህር አቡሃይ ውብሸት እንደሚለው ሥራውን እውን ለማድረግ ብዙ ተጉዟል። በተለይም በየአካባቢው ማሽኖችን አስቀምጦ የሙከራ ምርት ለማምረት ጥረት ሲደረግም ቆይቷል። ይሁን እንጅ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ምን ያክል ምርት ማምረት እንደሚያስችል አጥንቶ ትልቅ ማምረቻ ማሽን ለማስቀመጥ ጥናት ለማጥናት ባለበት ሂደት ላይ ሥራው መቆሙን ተናግሯል። ምክንያቱ ደግሞ ሥራውን የሚደግፍ በማጣቱ እንደኾነ መምህር አቡሃይ ውብሸት ነግረውናል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ ከአፈር ላይ ነዳጅ ማምረት የሚያስችለውን የምርምር ሥራን በተመለከተ አስፈላጊውን እገዛ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጿል። ምንም እንኳን በበጀት እጥረት ሥራው ቢጓተትም ሥራው ውጤታማ እንዲኾን አስፈላጊው እገዛ እንዲደረግ ራሱን የቻለ የሚያግዝ ዲፓርትመንት በማቋቋም እየሠራ እንደኾነም አመላክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ይህን ሥራ ብቻ ሳይኾን ሌሎችም በጅምር ያሉ ሥራዎች ውጤት ላይ ለማድረስ እየሠራ እንደኾነም ነው የገለጸው። ከዩኒቨርሲቲው በተጨማሪ ሌሎች የሚመለከታቸው ሁሉ እገዛ ቢያደርጉ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚያስችልም ተመላክቷል።
መሰል ሀገር የሚለውጡ ጥናቶችስ?
በእርግጥ ለአስረጅነት የመምህር አቡሃይ ውብሸት የጥናት ውጤትን አነሳን እንጅ በርካታ ሀገርን ሊቀይሩ የሚችሉ ጥናቶች አሁንም ሊታዩ የሚገባቸው ሥራዎች አሉ።
የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ ሲቋቋም አዳዲስ ፈጠራዎች ለማገዝ እንደኾነ የቢሮው ምክትል ኀላፊ የቻለ ይግዛው ነግረውናል።
ቢሮው የዲጂታል ዘርፉን ለማጠናከር፣ የመንግሥትን አገልግሎት አሰጣጥ ለማቀላጠፍ፣ ሕዝቡ ከመንግሥት ማግኘት የሚገባቸውን ግልጋሎት እንዲያገኝ ለማስቻል የሚያግዝ የሶፍትዌር ማልማት እና ለዚህም መሠረተልማት የመዘርጋት ሥራ በትኩረት ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል።
ቴክኖሎጅ ሲባል በዋናነት የሚመለከተው የፈጠራ ሥራን ነው። ፈጠራ ዋናው ለቴክኖሎጅ ሳንባው ስለኾነ እና ያለፈጠራ መሥራት ስለማይቻል ይህን መደገፍ ይጠይቃል፤ የቢሮው ሥራም ይሄው ነው ይላሉ።
በክልሉ ያሉ እና ቢሮው በተጨባጭ አውቋቸው እየተከታተላቸው ያሉ የፈጠራ ሥራዎች ላይ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ እንደኾነ ተናግረዋል።
ከትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር በዚህ ዓመት 17 ፕሮጀክቶች ቀርበው ሦሥቱ በክልሉ በተካሄደው ውድድር አሸናፊ በመኾናቸው ሽልማት መስጠታቸውንም ጠቁመዋል። የቴክኒክ ድጋፍም እያደረጉ እንደሚገኙም አስረድተዋል።
ምክትል ኀላፊው እንዳሉት በዚህ ዓመት የተሻለ የፈጠራ ሀሳብ ይዘው እንዲቀርቡ ወጣቶች እና ተማሪዎች ተጋብዘው ውድድር ተካሂዷል። ከሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የተሻለ ፈጠራ ያላቸውን 50 ፕሮጀክቶች በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥልጠና እንዲወስዱ መደረጉን ነው የነገሩን። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ሦሥት የተሻሉ የሚባሉትን ከ200 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር መሸለማቸውን ነው ያብራሩት።
ድጋፍ አላገኘንም የሚሉትስ እንዴት ይታያሉ?
በክልሉ አካባቢ በርካታ የተሻሉ ፈጠራዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ምክትል ቢሮ ኀላፊው ጠቁመዋል። ነገር ግን ቢሮው ጋር ካልደረሱ እና ካልታዩ የሚደገፉበት ዕድል ጠባብ ሊኾን ስለሚችል ወደ ቢሮው ቀርበው መታየት እና መገምገም እንደሚኖርባቸው ነው የነገሩን።
ለክልልም ይሁን ለሀገር የሚጠቅሙ የፈጠራ ሀሳቦች ወጥተው ሀገር እንዲጠቅሙ ስለሚፈለግ ወደፊት ወደ ቢሮው እየቀረቡ እና እየታዩ የሚደገፉበት አሠራር ይቀጥላልም ብለዋል።
ቢሮው ከመደገፍ ባለፈ ከግል ባለሃብቶች ጋር የማስተሳሠር ሥራው ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ቢሮው የሚሸልመው ሽልማት ሥራዎቹ ከፓይለት ወጥተው በሰፊው እንዲሠሩ ለማበረታታት እንደኾነ መገንዘብ ያስፈልጋል። አንዳንድ የፈጠራ ሥራዎች ግን ከፍ ያለ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቁ ሲኾኑ ከግል ባለሀብቶች ጋር የማገናኘት እና አብረው እንዲሠሩ የማድረግ ተግባር ይሠራል ነው ያሉት።
አንዳንድ የፈጠራ ባለሙያዎች ሥራዎችን በብቸኝነት ለመጠቀም ከመፈለግ በመነጨ ገንዘቡን ኢንቨስት ለሚያደርግ ማሳየት ላይ ፍቃደኛ ስለማይኾኑ ችግር እየተፈጠረ እንደኾነ አስረድተዋል።
ትልልቅ ሥራ ይዘው፣ በጋራ ራስንም ሌላውን መጥቀም እየተቻለ ሀገር የሚለውጡ ሥራዎች በፓይለት እንዲቀሩ ማድረግ መቆም እንዳለበትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን