
ባሕር ዳር፦ ሐምሌ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ መሪዎች እና ነዋሪዎች ጣናነሽ ፪ ጀልባን ለመቀበል ከየአደባባዩ ወጥተው ወደጀልባዋ አቅጣጫ እየተጓዙ ነው። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የከተማዋ መሪዎች እና ነዋሪዎች ለባሕር ዳር ከተማ ተደማሪ ውበት የምትኾነዋን ጀልባ ለመቀበል ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል ብለዋል።
ጣናነሽ ፪ አሁን ላይ ወደ ባሕር ዳር ከተማ እየተጠጋች መኾኗን እና ነዋሪዎችም ከመሪዎች ጋር በመኾን ወደዚያው እያመሩ ነው ብለዋል።
“ጣናነሽን በክብር መቀበል በፍቅር የሸኙልንን ኢትዮጵያውያን ማክበርም ነው” ያሉ ከንቲባው ጀልባዋ የመተሳሰብ፣ የአንድነት እና የፍቅር ተምሳሌት ናት ብለዋል።
ለታላቁ ጣና ሐይቅ እና ለባሕር ዳር ከተማ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና የምትጫዎት ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን