የኅብረተሰቡ ተሳትፎ የመንገድ ሥራ አብዮት ቀስቅሷል፡፡

13

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 25/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ የ022 ቀበሌ ነዋሪዎች በአቀበት እና ቁልቁለት ለዘመናት ሲቸገሩ ኖረዋል፡፡ ወጣት ያምራል ሙጨ እንደወገኖቹ የችግሩ ተጎጂ ነበር፡፡ ለገበያ፣ ለወፍጮ እና ለማኅበራዊ ግንኙነቶቻቸው በእግር እና በጋማ ከብቶች ሲጠቀሙ እንደኖሩ ይናገራል፡፡

ዘንድሮ ግን ከቀበሌው ወደ ፍላቂት ከተማ የሚያደርስ መንገድ ኅብረተሰቡ ሠርቷል፡፡ “እያንዳንዳችን አንድ ሺህ ብር አዋጥተናል፤ በጉልበትም አግዘናል” ያለው ወጣት ያምራል መኪናም ባይኖር እንደልባችን ወንዝ ተሻግረን መገናኘት ችለናል ብሏል፡፡

ከደብረታቦር – ርብ – መገንዲ – ሐሙስ ወንዝ መንገድ ሥራ ደግሞ በደቡብ ጎንደር ዞን ከሚሠሩ የሕዝብ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው፡፡

መንገዱ ከመሠራቱ በፊት ወላድ እናቶች በእንጨት እንደሚጓዙ፣ ደብረታቦር ለመድረስ 4 :00 ይፈጅ እንደነበር እና በወንዞች የተወሰዱ ሰዎችም በርካታ መኾናቸውን የመንገድ ሥራው የሕዝብ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ማሬ ታደሰ ጠቅሰዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ በ2015 ዓ.ም በተጀመረው ፕሮጀክት ተጠቃሚ ቀበሌዎችን በማስተባበር 1 ሚሊየን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡ የቤት ካርታ በማስያዝ ጭምር ማሽኖችን እስከመከራየት የደረሰ የኅብረተሰቡ መንገድ ልማት ጉጉት እና ጥረት መኖሩንም ነው የገለጹት፡፡

የመንገድ ሥራው መሰናክሎች ቢገጥሙትም በልማት ተቆርቋሪዎች ብርቱ ጥረት መገንባቱን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ቋሚ መኪና ባይመደብም ኅብረተሰቡ አልፎ አልፎ በተሽከርካሪ መጓዝ ጀምሯል፤ ደብረታቦር ገበያ ውሎ በባጃጅ መመለስ ችሏል ብለዋል፡፡ ሕዝቡም ደስተኛ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

መንገዱ ሲሠራም ኾነ ከተጠናቀቀ በኋላ በእንክብካቤ እንደሚጠቀምበት ተናግረዋል፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን መንገድ መምሪያ ኀላፊ ፀሐይነው ሲሳይ በዞኑ በኅብረተሰብ ተሳትፎ የተከናወኑት ሥራዎች ጉልህ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ በኅብረተሰብ ጉልበት እና ቁሳቁስ ብቻ 776 ኪሎ ሜትር መንገድ መሠራቱን አንስተዋል፡፡

ከ25 ሚሊየን ብር በላይ በማዋጣት 101 ኪሎ ሜትር መንገድ በማሽን መጠገኑን ኀላፊው ገልጸዋል፡፡ የወረዳ በጀትን ጨምሮ 68 ኪሎ ሜትር አዲስ መንገድም መሠራቱን ጠቅሰዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ የተመደበውን ካፒታል በጀት ጨምሮ ኅብረተሰቡ 78 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ጎንደር ዞን መንገድ መምሪያ ኀላፊ ዳግም ጥሩነህ በበኩላቸው በዞኑ የመንገድ ተደራሽነትን ለማሳደግ ለማኅበረሰብ ተሳትፎ በልዩ ትኩረት መሠራቱን ገልጸዋል፡፡ የኅብረተሰቡን 89 ሚሊየን ብር ጨምሮ ከምክር ቤቶች እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች 229 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።

በተሰበሰበው ሃብትም 359 ኪሎ ሜትር መንገድ በማሽን ተጠግኖ የ78 ቀበሌ ሕዝብ ተጠቃሚ መኾኑን ጠቅሰዋል። በሕዝብ ጉልበትም 770 ኪሎ ሜትር መንገድ ተጠግኗል ብለዋል፡፡

115 ኪሎ ሜትር መንገድ ደግሞ አዲስ መንገድ ተገንብቶ የ43 ቀበሌዎች ሕዝብ ተጠቃሚ ኾኗል ብለዋል፡፡ ሁሉም ሥራዎች ከእቅድ በላይ መፈጸማቸውን ነው የገለጹት።

የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) ለአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡት ሪፖርት በበጀት ዓመቱ በመንገድ ሥራ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ አበረታች መኾኑን ገልጸዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት 655 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን በላይ ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል። 500 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመሥራትም ታቅዶ 575 ኪሎ ሜትር መንገድ መሠራቱንም አመላክተዋል።

በገንዘብ መዋጮ የኅብረተሰቡ ድርሻ 56 በመቶ መኾኑን የጠቀሱት ኀላፊው ዘንድሮ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ መንገድ የመሥራት አብዮት ነው የተቀሰቀሰው ብለዋል።

8 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር መንገድም በሕዝብ መጠገኑን፣ ከ172 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ መደረጉን ተናግረዋል።

በቀጣይም በመንግሥት የኅብረተሰቡን መነሣሣት የሚመጥን በጀት መመደብ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየማኅበረሰቡን ጤና ለማሻሻል መከላከልን መሠረት ያደረገ የዘገባ ሽፋን መሥጠት ይገባል።
Next article“ጣናነሽን በክብር መቀበል በፍቅር የሸኙልንን ኢትዮጵያውያን ማክበርም ነው” ጎሹ እንዳላማው