የማኅበረሰቡን ጤና ለማሻሻል መከላከልን መሠረት ያደረገ የዘገባ ሽፋን መሥጠት ይገባል።

11

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሚዲያ ፎረም በ2017 በጀት ዓመት በተሠሩ ሥራዎች እና በቀጣይ በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።

የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) እንዳሉት በ2017 ዓ.ም መከላከል እና ማከም የጤና መርህን መሠረት ያደረገ የሚዲያ ሽፋን እንዲሠጥ ተደርጓል። በተለይም ደግሞ አስቸኳይ ምላሽ የሚያስፈልጋቸው የጤና ጉዳዮች ሲከሰቱ በወቅቱ ለሕዝብ ተደራሽ እንዲኾኑ ተደርጓል ነው ያሉት። በዚህም ማኅበረሰቡ የራሱን ጤና እንዲጠበቅ፣ በመንግሥት በኩል የታዩ እጥረቶች ደግሞ አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።

ፎረሙም በየጊዜው በመገናኘት ችግሮችን የማረም ሥራ እያከናወነ መኾኑንም ገልጸዋል። በቀጣይም የሚዲያ ተቋማት ማኅበራዊ የጤና እክል እንዳያጋጥም መከላከልን መሠረት ያደረገ የዘገባ ሽፋን መሥጠት ይገባቸዋል ብለዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ መልካሙ ጌትነት ሚዲያ በማኅበረሰብ የጤና ችግሮች ላይ ግንዛቤ በመፍጠር እና የመፍትሔ አቅጣጫ በመጠቆም ሚናው የጎላ መኾኑን ገልጸዋል። ባለፈው በጀት ዓመት መከላከል እና ማከምን መሠረት ያደረገውን የጤና ፖሊሲ ማኅበረሰቡ ተረድቶ ራሱን እንዲጠብቅ፣ ችግሩ ሲያጋጥም ደግሞ ፈጥኖ ሕክምና እንዲያገኝ የሚያስችሉ ሥራዎችን ሲሠሩ ቆይተዋል ነው ያሉት።

በጤናው ዘርፍ እየተሠሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው እና በዘርፉ የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ደግሞ አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ በቀጣይ ቅንጅታዊ አሠራር ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ታምራት ማለደ እንደገለጹት በ2017 በጀት ዓመት የሚዲያ ተቋማት ቅድመ መከላከል ላይ በሠሩት ሥራ ማኅበረሰቡ ራሱን ከተለያዩ በሽታዎች እንዲከላከል አድርጓል። በቀጣይ የኅብረተሰቡን የክትባት ፍላጎት ማሳደግ፣ እንደ የማሕጸን በር ካንሰር እና የጡት ካንሠር፣ ስኳር፣ ደም ግፊት፣ የልብ እና የአእምሮ ሕመም፣ የነርቭ እና የሱስ ችግር አጋላጭ ሁኔታዎች ላይ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የእቅድ ዝግጅት ክትትል ግምገማ ምክትል ዳይሬክተር ገብሬ ታረቀኝ አሚኮ የጤና ሥራዎችን በእቅድ በማካተት በሁሉም ማሰራጫዎች ሽፋን ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል። ከመደበኛው መርሐ ግብር ባለፈ በአጀንዳ ጭምር ትኩረት ሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

በ2017 በጀት ዓመት ከአሚኮ የጥቅል ዘገባዎች ውስጥ 25 በመቶ የሚኾኑት የማኅበራዊ ዘርፍ መኾናቸውን ያነሱት ምክትል ዳይሬክተሩ ከዚህ ውስጥ ደግሞ የጤናው ዘርፍ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ገልጸዋል። በ2018 በጀት ዓመትም አሚኮ በማኅበረሰቡ እሴት፣ በሰላም፣ በልማት እና በማኅበረሰቡ ጤና አጠባበቅ ላይ ትኩረቱን ያደርጋል ብለዋል።

የፎረሙ አባላት የጤና ቢሮው እያካሄደ ያለውን የመሥሪያ ቤት ሕንጻ እድሳት ጎብኝተዋል። በቢሮው እየተሠሩ የሚገኙ የማስፋፊያ እና የዲጅታላይዜሽን ሥራዎችም አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ትልቅ አቅም እንደሚኾን ተገልጿል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ለመትከል ያቀድነው ዕቅድ ከታሰበው በላይ ተሳክቷል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleየኅብረተሰቡ ተሳትፎ የመንገድ ሥራ አብዮት ቀስቅሷል፡፡